Fana: At a Speed of Life!

የስማርት ሜትር መሰረተ ልማት ዝርጋታ ማከናወን የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 6፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የስማርት ሜትር መሰረተ ልማት ዝርጋታ ለማከናወን የሚያስችል ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

ስምምነቱ የተፈረመው ኑሪ ቴሌኮም በተሰኘ የደቡብ ኮሪያ ኩባንያ እና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መካከል ነው።

ስምምነቱን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ፣ የአውቶሜሽንና ኢነርጂ ማኔጅምንት ሥራ አስፈፃሚ አቶ ደመቀ ሮቢ እንዲሁም የኑሪ ቴሌኮም ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ኪን ያንግሂዊ ተፈራርመውታል፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ የተፈረመው የስማርት ሜትር የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ስምምነት ለተቋሙ የገቢ ስብሰባ አስፈላጊና ወሳኝ በመሆኑ በፍጥነት ወደ ትግበራ ሊገባ ይገባል ብለዋል፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚው ተቋሙ በሙከራ ደረጃ የሚተገብረው ፕሮጀክቱ ዘመናዊ አሰራር ለመዘርጋትና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመዋል፡፡

ለዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቃት ያለውና ተወዳዳሪ ኩባንያ ተመርጦ ወደ ሥራ መገባቱን አንስተዋል፡፡

የኑሪ ቴሌኮም ማኔጂንግ ዳይሬክተር ኪን ያንግ ሂዊ በበኩላቸው÷ ፕሮጀክቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡

የስማርት ሜትር የመሰረተ ልማት ዝርጋታው የውል ስምምነት 2 ሚሊየን ስማርት ቆጣሪዎችን ማስተናገድ የሚችል የሲስተም ዝርጋታ ሲኖረው÷ በሙከራ ደረጃ ደግሞ 50 ሺህ ቆጣሪዎች በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚተከልበት ይሆናል ተብሏል፡፡

ከዚህ ውስጥ 5 ሺህ ያህሉ በኑሪ ቴሌኮም እንዲሁም ቀሪው 45 ሺህ ቆጣሪዎች ደግሞ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ይከናወናል፡፡

ፕሮጀክቱ የዲዛይን፣ የአቅርቦት፣ የኢንስታሌሽን እና የኮሚሽኒንግ ስራ የሚያካትት እንደሆነም ተገልጿል፡፡

ተግባራዊ የሚደረገው ስማርት ሜትር ፓይለት ፕሮጀክት ለከፍተኛ ሃይል ተጠቃሚ ደንበኞች ሲሆን የሃይል ብክነትን ለማስቀረትና የተቋሙን ገቢ ለማሳደግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.