Fana: At a Speed of Life!

‘ኢትዮሳት’ የአገሪቷ ብሮድካስተሮች በዓመት የሚያወጡትን 10 ሚሊየን ዶላር ወጪ በግማሽ መቀነስ ያስችላል-የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 6፣2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ‘ኢትዮሳት’ የአገሪቷ ብሮድካስተሮች በዓመት የሚያወጡትን 10 ሚሊየን ዶላር ወጪ በግማሽ መቀነስ የሚያስችል መሆኑን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን አስታወቀ።
ባለሥልጣኑ ብሮድካስተሮች በ’ኢትዮሳት’ በኩል ሥርጭት እንዲያደርጉ ለማስቻል የተሰራውን ሥራ አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር መግለጫ ሰጥቷል።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ እንዳሉት ለሰባት ወራት በተከናወነ ሥራ ኤስ.ኢ.ኤስ ከተባለ ሳተላይት አከራይ ኩባንያ ጋር ስምምነት ተፈርሟል።
በተደረገው ስምምነት መሰረትም የኢትዮጵያ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የ’ኢትዮሳት’ ሳተላይት ተጠቃሚ ይሆናሉ ነው ያሉት።
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት ገለጻ ይህ አሰራር የአገሪቷ የቴሌቪዥን ቻናሎች የተሻለ ተወዳዳሪ እንዲሆኑና የወጪ ጫናቸውንም መቀነስ ያስችላል።
የተመረጠው ሳተላይት አከራይ ድርጅትም በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች ተደራሽ የሚሆንና ጥራቱም የተሻለ መሆኑ መረጋገጡን ገልጸው ÷ ከብሔራዊ ደህንነት አንጻር ለሰላምና የአገራዊ እሴቶች በተሻለ መልኩ የሚንጸባረቁባቸው ጣቢያዎች እንዲኖሩም ያስችላል ብለዋል።
እስካሁን 60 የአገር ውስጥና የውጪ አገር ጣቢያዎች ሳተላይቱ ላይ መግባታቸውን የጠቀሱት ዶክተር ጌታቸው፤የዲሽ ሳህን ለማስተካከልና አድራሻውን ለመሙላት 20 ሺህ ወጣቶች ይሳተፋሉ ብለዋል።
እስካሁንም በቴክኒክና ሙያ ተቋማት በኩል 10 ሺህ ወጣቶች መሰልጠናቸውን ገልጸው፤ የአገልግሎት ክፍያቸውም ከ250 እስከ 350 ብር መሆኑን ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያ ብሮድካስተሮች ማህበር ተወካይ ዶክተር እንዳሻው ወልደሚካኤል በበኩላቸው፣ በየጊዜው እየጨመሩ ለመጡት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች መልካም እድል ነው ብለዋል።
ከዚህ በፊት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እጅግ ከሚፈተኑበት ችግር ውስጥም አንዱ የሳተላይት ኪራይ አገልግሎት ክፍያ መሆኑን ጠቅሰው ÷ ‘ኢትዮሳት’ የኢትዮጵያ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በዓመት ለሳተላይት ኪራይ የሚያወጡትን ክፍያ በግማሽ ይቀንስላቸዋል ነው ያሉት።
ይህ አሰራር የራሳቸው ኮሙዩኒኬሽንና ብሮድካስት ሳታላይት የሌላቸው አገሮች የሚጠቀሙበት መሆኑን ደግሞ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ ገልጸዋል።
ኢትዮሳት ከዚህ በፊት የሚያጋጠመውን የአገልግሎት ሽፋን ችግር መቀነስ የሚያስችል ከመሆኑም በላይ ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት መስጠት ያስችላልም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ የራሷን የብሮድካስት ሳታላይት ስታመጥቅ ያለተጨማሪ ወጪ አገልግሎቱ ተደራሽ እንዲሆን እድል የሚፈጥር መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ኤስ.ኢ.ኤስ የኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ መነን አገኙሁ በበኩላቸው ኢትዮሳት ‘የኢትዮጵያን ወደ ኢትዮጵያ’ ማለት መሆኑን ገልጸው ÷ ኢትዮሳት በህንጻዎችም ሆነ በዛፎች በተሸፈኑ አካባቢዎች ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት ያስችላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በአብዛኛው የ’ናይል ሳት’ ና የ’አረብ ሳት’ ሳተላይቶች ተጠቃሚዎች እንደነበሩ ይታወቃል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.