የሀገር ውስጥ ዜና

አየር መንገዱ ወደ መቐለ አቋርጦት የነበረውን በረራ ጀመረ

By Meseret Demissu

December 15, 2020

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 6፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ መቐለ አሉላ አባ ነጋ አውሮፕላን ማረፊያ አቋርጦት የነበረውን በረራ በዛሬው እለት በይፋ ጀመረ።

አየር መንገዱ በትግራይ ክልል በህወሓት ጁንታ ላይ ይወሰድ በነበረው የህግ ማስከበር ዘመቻ በረራውን አቋርጦ ቆይቷል።

ይሁን እንጂ የህግ ማስከበሩ ከተጠናቀቀ በኋላ በዛሬው እለት ምሽት ከአዲስ አበባ መንገደኞችን ጭኖ የመጀመሪያ በረራውን በማድረግ መቐለ አሉላ አባ ነጋ አውሮፕላን ማረፊያ ደርሷል።

ለመንገደኞችም የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ዶክተር አብርሃም በላይ፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አባል ጀኔራል ዮሐንስ ገብረ መስቀልና የጊዜያዊ አስተዳደሩ አስተባባሪ አቶ ሃፍታይ ገብረ እግዚአብሔር አቀባበል አድርገውላቸዋል።

መቐለ የደረሰው አውሮፕላን ሌሎች መንገደኞችን አሳፍሮ ምሽቱን ወደ አዲስ አበባ መመለሱ ታውቋል።

የአውሮፕላን ማረፊያው ሰራተኞችም በስራ ገበታቸው ላይ የተገኙ ሲሆን፣ በቀጣይ አየር መንገዱ በቀን ሁለት ጊዜ የሚያደርገውን በረራ ይቀጥላል በመባሉን ኢዜአ ዘግቧል።