ነባሩ ሥርዓተ ትምህርት በ2017 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ በአዲስ ሥርዓተ-ትምህርት እንደሚተካ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) ነባሩ ሥርዓተ – ትምህርት በ2017 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ በአዲስ ሥርዓተ -ትምህርት እንደሚተካ ተገለጸ።
በትምህርት ሚኒስቴር የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እሼቱ አስፋው እንደገለጹት፥ አሁን በስራ ላይ የሚገኘውን ስርዓተ – ትምህርት ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ በሙሉ በአዲስ ለመተካት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ነባሩን ሥርዓተ – ትምህርት ሙሉ በሙሉ በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ለመተካትና ተግባራዊ ለማድረግ የነባሩን ሥርዓተ – ትምህርት ጠንካራ ጎኖችና ያሉበትን ችግሮች በሚገባ ፈትሾ ከመለየት በተጨማሪ የሚሰሩ ሦስት ዋና ዋና ሥራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
ከሥራዎቹ መካከልም የሥርዓተ – ትምህርት ማዕቀፍ ዝግጅት፣ የመርሃ – ትምህርት ዝግጅት እና የመጽሃፍት ዝግጅት ይገኙበታል ነው ያሉት።
ሥራዎቹን በሦስት አመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑንም ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የዝግጅት ሥራውም የሁሉንም ክልሎች እና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ተወካይ ባለሙያዎችን በማሳተፍ እየተከናወነ መሆኑን ነው የገለጹት።
በአሁኑ ወቅት ከሦስቱ ዋና ዋና ሥራዎች መካከል ወሳኝና መሠረታዊ የሆነውን የሥርዓተ ትምህርት ማዕቀፍ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውንም ተናግረዋል።
በቀጣይ ጊዜያት በቅደም ተከተልና ጎን ለጎን የሚሠሩ ሥራዎችን በማጠናቀቅ በሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት የሚገመገም መሆኑንም አንስተዋል።
ከ2014 ዓ.ም ጀምሮም ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ባሉ የትምህርት ደረጃዎች ላይ ሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታን በሚገልጽ መልኩ ትምህርት ቤቶችንና ክፍሎችን በናሙናነት በመምረጥ የሙከራ ትግበራ ይከናወናል ብለዋል።