Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ በሱዳን ከገዳሪፍ ግዛት አስተዳዳሪ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 7፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ በሱዳን ከገዳሪፍ ግዛት አስተዳዳሪ ጋር በኢትዮጵያ እና ሱዳን ግንኙነት ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

በሱዳን የኢፌዴሪ ባለሙሉስልጣን አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ በሱዳን ከገዳሪፍ አስተዳዳሪ ዶ/ር ሱለይማን አሊ ጋር በገዳሪፍ ተገኝተው ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይቱም አምባሳደር ይበልጣል በአገራችን በትግራይ ክልል መንግስት ስለወሰደው ህግ የማስከበር እርምጃ እና ከዚህ ጋር ተያይዞ ወደ ሱዳን ስለገቡ ዜጎች፣ ስለጋራ ድንበር ፀጥታና በሁለቱ ሀገሮች በክልሎች ደረጃ ሊደረግ ስለሚገባቸው ትብብር አስረድተዋል፡፡

በዚሁ መሰረት ህግ የማስከበሩ ተግባር በአጭር ጊዜ በስኬት መጠናቀቁን፣ በአሁኑ ወቅት ወንጀለኞችን የማደን፣ የሲቪል አስተዳደሩን ወደ ስራ የመመለስ፣ የመሰረተ ልማት አውታሮችን የመገንባት እና ህገ-ወጥ ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታት ተግባራት በዋናነት እየተከናወኑ እንደሆኑ አብራርተዋል፡፡

ወደ ሱዳን የገቡ ዜጎች በተመለከተ ሱዳን ወደ ግዛቷ የገቡ ኢትዮጵያዊያንን ተቀብላ በማስተናገድ ረገድ የገዳሪፍ አካባቢ መስተዳድር እና ማህበረሰብ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናቸውን ገልፀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ሰላምና መረጋጋት የሰፈነ በመሆኑ ዜጎች ወደ ቀዬአቸው ይመለሱ ዘንድ የገዢውን ድጋፍ እና ትብብር ጠይቀዋል፡፡

በተጨማሪም አምባሳደር ይበልጣል የጋራ ድንበር ልማት ኮሚሽን መድረክን በመጠቀም በተጎራባች ክልሎች መካከል በመደበኛነት እየተገናኙ በልማት፣ ፀጥታ እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መስኮች መነጋገር እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የህገ-ወጥ የሰዎችና መሳሪያ ዝውውር እንዲሁም ህገ-ወጥ ንግድን በመቆጣጠር ጤናማ የንግድ እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባ አፅንዖት ሰጥተዋል፡፡

በጋራ ድንበር አካባቢ ጤናማ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይረጋገጥ ዘንድ የተጎራባች ክልሎች ሚና የጎላ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

የገዳሪፍ አስተዳደሪ ዶክተር ሱለይማን ሁለቱ ሀገሮች የቆየ ሁለገብ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን፣ በትግራይ ክልል የተካሄደውን የህግ ማስከበር እርምጃ ተከትሎ ሱዳን ድንበሯን በመዝጋት ቁጥጥሩን ማጠናከሯ፣ በአንፃሩ ደግሞ እርዳታ ለሚሹ ኢትዮጵያዊያን በሯን ክፍት አድርጋ ሌሎች ለጋሾች እስከሚደርሱ ድጋፍ ማድረጓን፣ በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ሰላም መረጋገጡ ለስደተኞች መመለስ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ መሆኑንና ለዚህም ስኬት የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል፡፡

አስተዳደሪው የድንበር አካባቢን ፀጥታን ለማረጋገጥ በጋራ መስራት እንዲሚገባ፣ ለዚህም የተጎራባች ክልሎች ሚና የጎላ መሆኑን፣ ኢትዮጵያና ሱዳን ለአካባቢው ብሎም ለአፍሪካ ሰላምና ዕድገት አስተዋፀኦ ማድረግ የሚችሉ ሀገሮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም ለሁለቱ ሀገሮች ግንኙነት መጠናከር ከኤምባሲው እና ከቆንስላ ጽ/ቤት ጋር ተቀራርበው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.