Fana: At a Speed of Life!

የሰሜን ዕዝ ሎጀስቲክ ኃላፊ ሜጀር ጀኔራል ከድር አራርሶ ፍርድ ቤት ቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 7፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሰሜን ዕዝ ሎጀስቲክ ኃላፊ ሜጀር ጀኔራል ከድር አራርሶ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ቀረቡ።

ተጠርጣሪው ህውሓትና ኦነግ ሸኔ ከተባሉ ጸረ-ሰላም ኃይሎች ጋር በመቀናጀት በአዲስ አበባና በተለያዩ አካባቢዎች ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል የመናድ ሙከራ እና የሃገር ክህደት ወንጀል በመፈጸማቸው ተጠርጥረው የምርመራ ጊዜ ተጠይቆባቸው እንደነበር ይታወቃል፡፡

ተጠርጣሪው መንግስት በትግራይ ክልል የነበረ የጦር መሳሪያ ወደ መሐል ሃገር እንዲመጣ ሲፈለግ መሳሪያው ከመቀሌ እንዳይወጣ የተቃወመና ሰዎችን ያደራጀ መሆኑንና ከቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ከነበሩት አብዲ ኢሌ ጋር በመሆን የኦሮሚያ ክልል ተወላጆችን እንዳስጨፈጨፉ ማስረጃ እንደለው ፖሊስ አስታውቋል፡፡

መርማሪ ፖሊስ ከተለያዩ የመንግስትና የግል ባንኮች የገንዘብ ልውጦችን ለማጣራት ፣ያልተያዙ ተጠርጣሪዎችን  በቁጥጥር ስር ለማዋል፣ ከያሉበት ለመያዝና ከተጠርጣሪዎቹ ጋር ያላቸውን የወንጀል ግንኙነት በማስረጃ ለመለየት ተጨማሪ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱም መርማሪ ፖሊስ ያቀረበውን ከሰማ በኋላ የተጠርጣሪውን ምላሽ ያዳመጠ ሲሆን ተጠርጣሪው ወንጀሉ ከተፈጸመበት ወቅት አስቀድሞ በሃምሌ 2012 ዓ/ም ጀምሮ ለህክምና ውጭ ሀገር እንደነበሩና የቀረበላቸውን ክስ የማይቀበሉት እንደሆነና የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ ተጠርጣሪው ያቀረበውን የዋስትና መብት ውድቅ አድርጎ ተጠርጣሪው ከተጠረጠሩበት ወንጀል  አንጻር  መረጃ  ሊያጠፋ ይችላል ብሎ ስላመነ መርማሪ ፖሊስ ከጠየቀው የ14 ቀን  የጊዜ ቀጠሮ  ውስጥ 8 ቀን በመፍቀድ ለታህሳስ 15 ቀን 2013 ዓ/ም መርማሪ ፖሊስ መረጃውን አጠናክሮ እንዲመጣ ችሎቱ ማዘዙን ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.