Fana: At a Speed of Life!

ጁንታው ሰነዶችን ለማጥፋት ታራሚዎችን በመቐለ ከተማ ውስጥ በመልቀቅ ዝርፊያ እንዲፈጸም ማድረጉን የከተማዋ ከንቲባ አቶ አታክልቲ ኃይለስላሴ ገለፁ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 8፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህወሓት ጁንታ በትግራይ ክልል ባሉ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ የነበሩ የህግ ታራሚዎችን ሰብስቦ በመቐለ ከተማ ውስጥ በመልቀቅ ዝርፊያ እንዲፈጸም ማድረጉን የከተማዋ ጊዜያዊ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አታክልቲ ኃይለስላሴ ገለፁ፡፡

በመንግሥት የተወሰደውን የህግ ማስከበር ዕርምጃ ተከትሎ የጁንታው አባላት በክልሉ የተለያዩ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ በተለያዩ ወንጀሎች ተይዘው የእስር ጊዜያቸውን እየፈጸሙ የነበሩ ታራሚዎችን መቐለ ከተማ ለቀዋቸዋል።

በዚህም በከተማዋ ውስጥ የዝርፊያ ወንጀል እንዲፈጽሙና ህዝቡ በስጋት ውስጥ እንዲወድቅ አድርገዋል ብለዋል አቶ አታክልቲ።

በበርካታ ወንጀሎች ተይዘው የነበሩ ሰዎችን በከተማዋ ውስጥ በመልቀቅ የግለሰቦች ሱቅ ጭምር እንዲዘረፉ ተደርጓልም ነው ያሉት፡፡

ይህን ያደረጉት አንድም ተቋማትን በመዝረፍ ሰነዶችን ለማጥፋት፣ ሁለትም ሕዝቡ ወደ ስጋት እንዲገባና እንዲጠራጠር በማድረግ በመከላከያ ሠራዊቱ እና በአዲሱ አስተዳደር ላይ እምነት እንዲያጣ ለማድረግ መሆኑንም አስረድተዋል።

በዚህም ብዙ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ሆን ተብለው እንዲዘረፉ ተደርጓል ብለዋል አቶ አታክልቲ ኃይለስላሴ፡፡

በከተማዋ የታየው ዝርፊያ በጁንታው ትዕዛዝ የተፈጸመ መሆኑን በመግለጽም፤ በተለይ በዋና ዋና መስሪያ ቤቶች ላይ ራሳቸው እዚያ ይሠሩ የነበሩ ሰዎች አንዳንድ ሰነዶችን ያጠፉበት መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ የከተማ አስተዳደሩ የከንቲባ ጽሕፈት ቤት አስተዳደር ሙሉ ለሙሉ መዘረፉን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የሕዝብ አገልግሎት መስጫዎች የሆኑት የፍትህ ተቋማት፣ ማዘጋጃ ቤት፣ ፍርድ ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ሰነዶች ተዘርፈዋል ያሉት አቶ አታክልቲ፥ በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ሆን ተብሎ የተቀናጀ ዝርፊያ ከተፈጸመ በኋላ ተሰርቆ ነው ለማለት ተቋማቱን ክፍት አድርገው መተዋቸውንም አስረድተዋል።

ይህንን አጋጣሚ የተጠቀሙ ሌሎች ዘራፊዎችም የተለያዩ ቁሳቁሶችን መዝረፋቸውንም ጠቁመዋል።

አሁን ከተማዋ ወደ ዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዋ እየተመለሰች መሆኗን የሚያሳዩ ጥሩ እንቅስቃሴዎች አሉ ያሉት አቶ አታክልቲ፤ ህብረተሰቡን ያማከለ ሥራ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን እየተሠራ ስለሆነ በአጭር ቀናት ውስጥ መቐለ ወደነበረችበት መደበኛ እንቅስቃሴ እንደምትመለስ አረጋግጠዋል።

ለዚህም በከተማ ደረጃ በምናቋቁመው ምክር ቤት ሕዝቡ በቀጥታ የሚመርጣቸው የየትኛውም ፖለቲካ ፓርቲዎች አባል የሆኑና ለውጡን ደግፈው ሕዝቡን ወደ ተሻለ ደረጃ ሊያሸጋግሩ የሚችሉ አካላት ወደኃላፊነት ይመጣሉ ብለዋል፡፡

አሁን የተፈጠረውን ጊዜያዊ ምስቅልቅል በመቆጣጠርና በመምራት ኃላፊነት ወስደው የሚሠሩ፣ ሕዝቡም የተቀበላቸው እና ጥሩ ስነምግባር ኖሯቸው በሕብረተሰቡ አካባቢ ያለውንና የሚነሱትን የፍትህ፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ በፍቃደኝነት መሥራት የሚችሉ ሰዎች በሙሉ የሚካተቱበት ዕድል እንዳለ መናገራቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.