Fana: At a Speed of Life!

ከባህርዳር ከተማ የሚወጣው ፍሳሽ ቆሻሻ ከ70 እስከ 80 በመቶው በቀጥታ ወደ ጣና ሐይቅ ይገባል – ጥናት

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 8፣ 2013(ኤፍቢሲ) ከባህርዳር ከተማ የሚወጣው ፍሳሽ ቆሻሻ ከ70 እስከ 80 በመቶው በቀጥታ ወደ ጣና ሐይቅ እንደሚገባ በአንድ ጥናት ተመላክቷል፡፡

በአማራ ክልል ከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ አስተባባሪነት ከባህርዳር ከተማ አስተዳደር ወሰን “የጣና ሐይቅ ዳርቻ የልማት ስራዎች ተፅዕኖ እና አማራጭ የልማት ስራዎች” ጥናት ቀርቦ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሄዷል፡፡

በውይይቱ ጥናቱን ያቀረቡት የአካባቢ፣ ደን እና ዱር እንሳሳት ጥበቃ እና ልማት ባለስልጣን የአካባቢና ማህበረሰብ ተፅዕኖ ዳይሬክተር አቶ አበባው አባይነህ ከተማዋ ፈሳሽ ቆሻሻ ከ6 በላይ በሚሆኑ በሮች ከ70 እስከ 80 በመቶ ፍሳሽ ቆሻሻ ወደ ሐይቁ የሚገባ መሆኑን በጥናታቸው ያረጋገጡት፡፡

ፍሳሽ ቆሻሻው ከፍተኛ መጠን ያለው ናይትሮጅንና ፎስፈረስ ክምችት እንዲሁም የበሽታ አምጭ ተህዋስያንና የተለያዩ ኬሚካሎች ወደ ሐይቁ እየገባ ነው ተብሏል፡፡

ወደ ጣና ሐይቅ የሚገባው ፈሳሽ ቆሻሻ የሐይቁን ብዝኀ-ህይወት የማጥፋት አደጋ መፍጠሩም ተገልጿል፡፡

ተፅዕኖውን ለመከላከል ወደ ሐይቁ የሚገባን የኬሚካል ልቀት ለማስቀረት፣ የተፋሰስ ልማት ማስኬድና የአካባቢውን ተፈጥሯዊ ደህንነት ሊያስጠብቁ የሚችሉትን መለየት እንደመፍትሔ በጥናቱ ተቀምጧል፡፡

ከዚህ ባለፈ በከተማዋ የሚገነቡ ግንባታዎች ከሐይቁ በ50ሜትር ርቀት እና ከዚያ በላይ መራቅ አለባቸው ተብሏል፡፡

በናትናኤል ጥጋቡ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.