Fana: At a Speed of Life!

የሀረሪ ክልል በኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 8 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ መርቻው የተመራ የልዑካን ቡድን ከሃረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሚስራ አብደላ ጋር ተወያይቷል።

የልዑኩ ጉብኝት በከተሞች መካከል ቀድሞ የነበረውን ግንኙነት ለማጠናከርና ከቱሪዝም ሴክተሩ ጋር ለማስተሳሰር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

በወቅቱም ከተሞች ተደጋግፈው ሊያድጉ በሚችሉባቸው ሁኔታዎች፣ በቱሪዝም ዘርፉ ጥበቃና እንክብካቤ ላይ በትብብር ለመስራት ተመክሯል።

ባህላዊ ቅርሶችና ታሪካዊ ስፍራዎችን እንዲሁም በግብርናው ዘርፍ ክልሉ የሚታወቅባቸውን እንደ ቡናና የተለያዩ የአትክልት ምርቶችን ማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ ተናግረዋል።

የክልሉን ሰላም በመጠበቅ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ለሚመጡ ባለሀብቶች የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልፀዋል።

አምባሳደር ሬሚ በበኩላቸው በክልሉ አሁን ላይ ያለውን ሰላምና መረጋጋት አድንቀዋል።

በቀጣይ ቀናትም በክልሉ እንደ አርተር ራንቦ ሙዚየም የመሳሰሉትን ታሪካዊ ስፍራዎች ጨምሮ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ የመስክ ምልከታ እንደሚያደርጉ ከሀረሪ ክልል ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

የልዑካን ቡድኑ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በመገኘት ከአመራሩ ጋር የወደፊት የትብብር መስኮች ዙሪያ ላይ ውይይት ያደረገ ሲሆን በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማቶችን ጎብኝቷል፡፡

በኮቪድ 19 ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የፈረንሳይኛ ቋንቋ ትምህርት ለማስጀመርም ስምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው ለሚያከናውናቸው ተግባራት በትብብር ለመስራት የሚቻልበት ሁኔታዎችን እንደሚያመቻቹም ተገልጿል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.