Fana: At a Speed of Life!

በሱዳን ምዕራብ ዳርፉር በተፈጸመ ጥቃት የ24 ሰዎች ህይዎት አለፈ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23፣ 2012(ኤፍቢሲ) በሱዳን ምዕራብ ዳርፉር በስደተኞች መጠለያ ካምፕ በተፈጸመ ጥቃት በጥቂቱ 24 ሰዎች መሞታቸው ተነገረ።

ከሟቾቹ ውስጥ ህጻናትና ሴቶች የሚገኙበት ሲሆን፥ ከሞቱት በተጨማሪ ከ100 በላይ ስደተኞች መጎዳታቸም ነው የተነገረው።

በስፍራው የሚንቀሳቀሱ የረድኤት ድርጅቶች ደግሞ የሟቾቹን ቁጥር እስከ 40 ያደርሱታል።

ጥቃቱ የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በሚያስተናግደው መጠለያ ካምፕ የዓረብ ጎሳ አባላት በካምፑ በሚገኙ የአፍሪካ ጎሳ አባላት ላይ የፈጸሙት መሆኑን፥ በዳርፉር የተሰማራው የተመድና የአፍሪካ ህብረት ጥምር ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ቃል አቀባይ አሽረፍ ኢሳ ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ ባለፉት ቀናት የዓረብ ጎሳ አባላት ወደ መጠለያ ካምፑ በመግባት በአፍሪካ ጎሳ አባላት ላይ የተኩስ ጥቃት መፈጸማቸውን እና ንብረቶች ማውደማቸውንም ተናግረዋል።

ጥቃት ፈጻሚዎቹ የተፈጠረውን ግጭት ለማብረድ ወደ ስፍራው ያቀና የፖሊስ አባል መግደላቸውንም ቃል አቀባዩ አስረድተዋል።

ከጥቃቱ በኋላ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርና የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ወደ ስፍራው በማቅናት ሁኔታውን በተመለከተ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።

ከቀድሞው የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ኦማር ሃሰን አልበሽር ከስልጣን መወገድ ወዲህ በዳርፉርና በአንዳንድ አካባቢዎች ሰላምን ለማስፈን የሚደረገው ጥረት ስኬት አለማምጣቱ ይነገራል።

በዳርፉር የሚገኙ ታጣቂዎችም ከመንግስት ጋር እያደረጉት የነበረውን የሰላም ድርድር ማቋረጣቸው ይታወሳል።

ታጣቂዎቹ በሃገሪቱ በተፈጠሩ የጎሳ ግጭቶች ላይ ተገቢው ምርመራ እንዲደረግ ተፅዕኖ ለመፍጠር በማሰብ የሰላም ድርድሩን ማራዘማቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።

ምንጭ፦ አልጀዚራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.