የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎትን የዲጂታል አሰራር የማሻሻል ስራ  ሊጀመር ነው

By Meseret Demissu

December 18, 2020

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 9 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከጀርመን የኢኮኖሚ ጉዳዮች  እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር የኢትዮጵያ ፖስታ አገልገሎት የዲጂታል አሰራርን  ለማዘመን በጋር ለመስራት ተስማምተዋል።

በስምምነቱ መሰረት የጀርመን የኢኮኖሚ ጉዳዮች  እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ድጋፎችን ያደርጋል ነው የተባለው።

በሁለቱ ሚኒስቴር መስሪያቤቶች በተደረሰው ስምምነት መሰረት የድጋፍ ስራው በየካቲት ወር መጀመሪያ እንደሚጀመርም ነው የተገለጸው።

በውይይቱ ላይ ከሁለቱ ሚኒስቴር መስሪያቤት  የስራ ሃላፊዎች ፣የጀረመን ፖስታ አገልገሎት እና የኢትዮጵያ ፖስታ አገልገሎት ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያፀደቀችው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን  ስትራቴጂ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የኢኮሜርስ አገልግሎትን ማስፋፋትመሆኑም ተመላክቷል።

ኢኮሜርስን ለመተግበር ደግሞ ዘመናዊ የፖስታ አሰራር ወሳኝ ድርሻ አለውም ነው የተባለው፡፡

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎትን የዲጂታል አሰራርን የማሻሻል ስራ ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂው ስኬት ወሳኝ ድርሻ አለው መባሉን ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡