በውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት የሚስተዋሉ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል የቅንጅት መድረክ ተቋቋመ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትን በመሳብ ሂደት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል የቅንጅት መድረክ ተቋቋመ።
የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትን በመሳብ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ውይይት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተባባሪነት በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በአሁኑ ሰዓት እየተካሄደ ያለውን አጠቃላይ ሀገራዊ ለውጥ ተከትሎ በርካታ የውጭ ባለሃብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን በኢትዮጵያ ለማፍሰስ በስፋት እየመጡ መሆኑን አንስተዋል።
ይሁን እንጅ ባለሀብቶችን በአግባቡ ተቀብሎ በማስተናገድ እና ወደ ስራ በማስገባት በኩል ክፍተቶች መኖራቸውን ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።
በመሆኑም የሚታዩ ችግሮችን በአግባቡ በመፍታት የተሻለ ኢንቨስትመንት ለመሳብ እንዲቻል ችግሮችን በቅርብ እየተከታተለ የሚፈታ መድረክ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዚህም መሰረት የማክሮ ኢኮኖሚ ቡድን አባላት፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ቦርድ አካላት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ያካተተ ውይይት ለማካሄድ መድረኩ መጠራቱን አስረድተዋል።
በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ በበኩላቸው፥ በበአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን በዓለም ላይ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ የሚያደርጓት ምክንያቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት በርካታ ባለሃብቶች እየመጡ መሆኑን ገልጸዋል።
የውጭ ባለሀብቶች የሚያጋጥማቸውን ችግር እንደ ሀገር የመፈጸም አቅማችንን በማሳደግ መፍታት እንደሚያስፈልግም አምባሳደር ግርማ አሳስበዋል።
የውጭ ባለሃብቶችን ወደ ኢንቨስትመንት ከማስገባት አንጻር ከምልመላ ጀምሮ፣ በቅድመ ኢንቨስትመንት እንዲሁም ከኢንቨስትመንት በኋላ በርካታ ችግሮች እንደሚያጋጥሙ በውይይቱ ተመላክቷል።
ከዚህ ባለፈም ባለሀብቶች ወደ ስራ ከገቡ በኋላ ከጸጥታ እና ደህንት፣ ከመሰረተ ልማት አለመሟላት፣ ከውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ ከታክስ ጋር የተያያዙ ችግሮች፣ ከመሬት አቅርቦት፣ ከውጭ ባለሙያዎች ፈቃድ አሰጣጥ፣ የተንዛዛ አሰራር እና ሌሎች ከሎጂስቲክስ ጋር የተያያዙ ችግሮች እንደሚያጋጥማቸው ተገልጿል።
ችግሩን በቋሚነት በቅርብ ለመከታታል እንዲቻል ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የሴክተር መስሪያ ቤት ሃላፊዎች ያካተተ የቅንጅት መድረክ ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑም መግባባት ላይ ተደርሷል።
በዚህ መሰረትም በአምባሳደር ግርማ ብሩ የሚመራ የቅንጅት መድረክ የተቋቋመ ሲሆን፥ የመድረኩ ቀጣይ ስብሰባም በጥር ወር 2012 ዓ.ም መጨረሻ እንዲካሄድ መወሰኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።