Fana: At a Speed of Life!

የአምባሳደር ስዩም መስፍን የትዳር አጋር እና ልጃቸው ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 9፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአምባሳደር ስዩም መስፍን የትዳር አጋር ወይዘሮ ፈለገህይወት በርሔና ልጃቸው አጋዚ ስዩም ለሁለተኛ ጊዜ  በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ሁለተኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ላይ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው ስምንት ቀን ውስጥ የሰራቸውን የምርመራ ስራዎች ለችሎቱ ይፋ አድርጓል፡፡

ቃል መቀበሉን፣ በቤታቸው የተገኙ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ለቴክኒክ ምርመራ መላኩን እና ውጤቱን እየጠበቀ መሆኑን የተናገረው መርማሪ ፖሊስ በተጠረጠሩበት የወንጀል ተሳትፎ በምስክር የማስመረጥ ስራ እና በመኖሪያ ቤታቸው የተገኘውን የባንክ ደብተር ተከትሎ የገንዘብ ምንጫቸውን ማጣራት እና በመኖሪያ ቤታቸው የተገኘን ሁለት ሽጉጥ ህጋዊነት የማጣራት ስራ እየሰራ መሆኑን ገልፆ ከወንጀሉ ውስብስብነት አንፃር ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ 14 ቀን ይሰጠኝ ሲል ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በተለይም የአምባሳደር ስዩም መስፍን የትዳር አጋር ወይዘሮ ፈለገህይወት ሰኔ 28 ቀን የመንግስት የኪራይ ቤቶች የነበረን ቤት ታሽጎ እና በተደረገ ብርበራ የተገኘ ሽጉጥ ራሴ ሄጄ ፖሊስ ጣቢያ እንዲመዘግቡልኝ እና በወቅቱ ልፈርም ስል ቤቱ ከተፈተሸ በኋላ ትፈርሚያለሽ በሚል ምክንያት አልፈረምኩም ብለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በቂ አድራሻ እንዳላቸው በመጥቀስም የእርሳቸውም ሆነ የልጃቸው የጤንነት ሁኔታ ችግር ላይ ነው በማለት፤ የደም ግፊታቸው መጨመሩን በማንሳትም በድጋሚ መድኃኒት እንዳመጣ ይፈቀድልኝ ፤ ልጄም ካለው የጤና ሁኔታ አንጻር በዋስ ወጥተን ከቤተሰብ ጋር ይቀመጥልኝ ሲሉ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡

ጉዳዩን የተከታተለው ፍርድ ቤቱ መዝገቡን በተመለከተ ምርመራው በጥቅል  እየቀረበ መሆኑን በመጥቀስና ትዕዛዝ ለመስጠትም ተሳትፏቸው ተነጥሎ ይቅረብ በማለት ምርመራው እንዲቀጥል ለመርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ 10 ቀን ፈቅዶለታል፡፡

ለጤናቸው የሚውል  አስፈላጊ መድሃኒትም ታጅበው እንዲያመጡ ፈቅዶላቸዋል፡፡

 

በታሪክ አዱኛ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.