Fana: At a Speed of Life!

ተፈናቃይ በመምሰል በሽሬ ከተማ ሲንቀሳቀስ የነበረው የጁንታው አመራር በቁጥጥር ስር ዋለ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 9፣ 2013 (ኤፍቢሲ) በባዕከር፣ በሁመራና በቃፍታ አካባቢዎች የሚሊሻ ዋና አስተባባሪ በነበረበት ወቅት በንጹሃን ላይ ግፍ ፈጽሟል ተብሎ የተጠረጠረ ግለሰብ በሽሬ ከተማ በቁጥጥር ስር መዋሉን የሀገር መከላከያ ሰራዊት አስታወቀ።

የ5ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር የብረት ለበስ አዛዥ ሻምበል አማኑኤል በለጠ÷ እንኳአየነው መሰለ የተባለው ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር የዋለው ተፈናቃይ በመምሰል በሽሬ ከተማ ሲንቀሳቀስ ነው ብለዋል።

ግለሰቡ በባዕከር፣ ሁመራና ቃፍቲያ አካባቢ የሚሊሻ ጽህፈት ቤት ሃላፊና የፀጥታ ዘርፍ አስተባባሪ በመሆን የጁንታው የጥፋት ተልዕኮ ሲያስፈጽም መቆየቱንም ነው የገለጹት።

የህወሓት ጁንታ በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከመፈጸሙ አራት ቀናት ቀደም ብሎ  “ሰራዊቱ በወለጋና በትግራይ ክልል ጭፍጨፋ እያካሄደ ነው” በሚል የሀሰት መረጃ  በማሰራጨት የጥፋት ቅስቀሳ ሲያካሂድ እንደነበርም ተናግረዋል።

የጁንታውን ሚሊሻዎች በማስተባበር መከላከያ ሰራዊቱ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም በማድረግ ረገድም ጉልህ ሚና እንደነበረውም ጠቁመዋል።

በክፍለጦሩ የሁለተኛ ብርጌድ አባል ሃምሳ አለቃ ምህረት ደምሌ በበኩላቸው ተጠርጣሪው ከዚህ ቀደም ስልጣኑን በመጠቀም በተለይ አማራ ተወላጆች ላይ ማንነትን መሰረት ያደረገ ጭቆና ሲፈፅም መቆየቱን ተናግረዋል።

“የፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ መለያን ለብሳችኋል እንዲሁም ‘የእገሌን’ ሙዚቃ አዳምጣችኋል” በሚል ምክንያት በንጹሃን ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመፈጸም የሚፈለግ ተጠርጣሪ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በአካባቢው የተለያዩ የፍተሻ ጣቢያዎችን በማቋቋም የሀገር መከላከያ ሰራዊት መደበኛ እንቅስቃሴን  ሲያስተጓጉል መቆየቱንም ጠቅሰዋል።

ሻምበል አማኑኤል እና ሃምሳ አለቃ ምህረት ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር በማዋል ረገድ የአካባቢው ማህበረሰብ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

የአካባቢው ማህበረሰብ በቀጣይ ሌሎች ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ  በሚደረገው ጥረት ላይ የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

መንግስት በጽንፈኛው የህወሃት ጁንታ ሲያከናውን የነበረውን የህግ ማስከበር ዘመቻ አጠናቆ ወንጀለኞችን የማደንና ማህበረሰቡን መልሶ የማቋቋም ምዕራፍን እየተገበረ እንደሚገኝ ይታወቃል።

 

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.