የሀገር ውስጥ ዜና

የባህርዳር አውሮፕላን ማረፊያ “የባህርዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ አውሮፕላን ማረፊያ” ተብሎ እንዲጠራ ተወሰነ

By Feven Bishaw

December 18, 2020

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 9፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት አመታት “የባህርዳር ግንቦት 20 አውሮፕላን ማረፊያ” ተብሎ ይጠራ የነበረው የባህርዳር አውሮፕላን ማረፊያ”የባህርዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ አውሮፕላን ማረፊያ” ተብሎ እንዲጠራ ተወሰነ፡፡

ባለፉት አመታት “የባህርዳር ግንቦት 20 አውሮፕላን ማረፊያ” ተብሎ ይጠራ የነበረው የባህርዳር አውሮፕላን ማረፊያ በህብረተሰቡ ፍላጎት ውይይት ሲደረግበት ቆይቶ ዛሬ የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባ ነው “የባህርዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ አውሮፕላን ማረፊያ” ተብሎ እንዲጠራ የተወሰነው ።

ይህ ስያሜ ከ1983 ዓ.ም በፊትም ይጠራበት እንደነበር ያስታወሰው የከንቲባ ኮሚቴው የህዝቡን ፍላጎትና የከተማውን ወካይ ስያሜ በመምረጥ ስሙ እንዲቀየር በሙሉ ድምፅ ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቋል።

ተቋርጦ የነበረው የበረራ አገልግሎት ከነገ ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ አገልግሎቱን እንደሚጀምር አስተባባሪ ኮሚቴው መግለፁን ከአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡