በትራንስፖርት ሚ/ር ወ/ሮ ዳግማዊት የተመራው ልዑክ በሱዳን የነበረውን የስራ ጉብኝት አጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ የተመራው የልዑካን ቡድን በሱዳን ካርቱም የነበረውን የስራ ጉብኝት በስኬት አጠናቋል።
ልዑኩ በካርቱም ቆይታውም ከሀገሪቱ የመሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ሚኒስትር ኡመር አህመድ መሃመድ፣ የፖርት ሱዳን ኮርፕሬሽን ዋና ዳይሬክተር ካፕቴን አንዋር ሙሳ እንዲሁም ከንግድና፣ ከፋይናንስ ሚንስትርና ከጉሙሩክ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር ተወያይቷል።
በውይይታቸው ሀገራቱን በትራንስፖርት ለማስተሳሰር፣ በወደብ አጠቃቀም እና በዘርፉ የተደረጉ ስምምነቶችን መተግበር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ መክረዋል ።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ፖርት ሱዳንን ስትጠቀም ያጋጥሙ የነበሩ ማነቆዎችን በጋራ መፍታት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከስምምነት ላይ መድረስ መቻሉም ተመላክቷል።
በተጨማሪም በምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኙ አካባቢዎች ፖርት ሱዳንን በመጠቀም የወጪ ገቢ ንግድ ፍሰትን ለማሻሻሻል በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ መምከራቸው ነው የተገለጸው።
በሌላ በኩል ማዳበሪያና ሌሎች ምርቶች ወደቡን በመጠቀም ለማስገባት በሚቻልበት ሁኔታ ከመሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ሚኒስትርሩ እንዲሁም ተጠሪ ከሆኑ መስሪያ ቤቶች መካከል የሱዳን የባህር ወደብ ባለስልጣን፣ ከሱዳን ምድር ባቡር፣ ከሱዳን መንገዶች ባለስልጣን ኃላፊዎች ጋር ውይይት ተካሂዷል።
በቅርቡ ለሚጀመረው ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ የማስገባት ሂደትን እንዲያግዝም የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርና ሎጅስቲክ አገልግሎት ድርጅት ማስተባበሪያ ቢሮ በኮርፖሬሽኑ በኩል ለማዘጋጀት ስምምነት ላይ ተደርሷል።
በስራ ጉብኝቱ ከተለያዩ የስራ ሃላፊዎች ጋር በኮሪደሩ የተሰሩና በሂደት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች ያሉበትን ደረጃ በተመለከተ እንዲሁም በወደብ አገልግሎትና አጠቃቀም ዙሪያ ውጤታማ ውይይት መካሄዱን ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ምክክሩን መሰረት በማድረግ የሱዳን ባህር ወደብ ኮርፖሬሽን ኢትዮጵያ ለገቢና ወጭ ንግድ ዕቃዎች የሱዳንን ወደብ ስትጠቀም አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ የፖርት ሱዳን ኮርፕሬሽን ዋና ዳይሬክተር ካፕቴን አንዋር ሙሳ ገልጸዋል።
ከዚህ ባለፈም የወደቡን አጠቃቀም ለማሳለጥና ቴክኒካል ጉዳችን የሚሰራ ኮሚቴ ለማቋቋም ከስምምነት የተደረሰ ሲሆን፥ ኮሚቴውም በአስራ አምስት ቀናት ውስጥ የመጀመሪያውን ስብሰባ እንዲያካሂድ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
በ19 95 ዓ. ም የሱዳን መንግስት ለኢትዮጵያ ሎጅስቲክ አገልግሎት እንዲውል በወደቡ አቅራቢያ የሰጠውን 875 ሺህ ካሬ ሜትር በአግባቡ ርክክብ ተደርጎ አገልግሎት ላይ ያልዋለ በመሆኑ አስፈላጊውን ሁኔታ በማቻቸት ቦታውን አገልግሎት ላይ ለማዋልም ተስማምተዋል።