Fana: At a Speed of Life!

ጅማ ዩኒቨርሲቲ በሀገር አቀፍ ደረጃ ትኩረት በተሰጣቸው የትምህርት ዘርፎች ምሁራንን ለማፍራት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 10፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ጅማ ዩኒቨርሲቲ በሀገር አቀፍ ደረጃ ትኩረት በተሰጣቸው የትምህርት ዘርፎች 5 ሺህ ፒ.ኤች.ዲ ምሩቃንን ለማፍራት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

በምርምር፥ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲነት የተመረጡ 10 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በበርካታ ዘርፎች ስልጠና ለመስጠት ተለይተው መዘጋጀታቸው ተገልጿል፡፡

በጅማ ዩኒቨርሲቲ ከፒ.ኤች.ዲ እስከ ሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ባላቸው ምሁራን መካከል ውይይት ተካሄዷል፡፡

በውይይቱም በሀገር አቀፍ ደረጃ ትኩረት በተሰጣቸው የትምህርት ዘርፎች 5 ሺህ ፒ.ኤች.ዲ ምሩቃንን ለማፍራት እየተሰራ ነው ተብሏል፡፡

የግብርና፣ ማምረቻ፣ የማእድን፣ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ እና የቱሪዝም ዘርፎች በሀገር አቀፍ ደረጃ ቅድሚያ የተሰጣቸው የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውም ነው የተገለጸው፡፡

በፈረንጆቹ ከ2021 እስከ 2025 ባሉት አምስት አመታት 5 ሺህ በፒ.ኤች.ዲ. ደረጃ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ለማፍራት ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ በመጀመሪያዎቹ ሁለት አመታት ሰልጣኞችን ተቀብለው ማሰልጠን እንደሚጀምሩ ተገልጿል።

የአግሮኖሚ፣ ሂውማን ኒውትሬሽን፣ ሴራሚክ ኢንጂነሪንግ፣ ኢንዱስትሪያል ኢኮኖሚክስ እና ኢኮ-ቱሪዝም ጅማ ዩኒቨርሲቲ በሆስትነት የተመረጠባቸው ዋነኛ ዘርፎች እንደሆኑ በውይይት መድረኩ ተነስቷል፡፡

በመድረኩ በርካታ ሃሳቦች ተነስተው ዉይይት የተደረገባቸው ሲሆን መድረኩ የተለያዩ ግብረ-መልሶች የተሰበሰቡበት እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

የውይይት መድረኩን የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ታደሰ ሀብታሙ የመሩት ሲሆን የዩኒቨርሲቲው የድህረ ምረቃ ፕሮግራም ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተፈራ በላቸው የውይይት መነሻ ሀሳብ ለተሳታፊዎች ማቅረባቸውን ከዩኒቨርሲቲው ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.