Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ዘነቡ ከጣሊያን ሪፓብሊክ ፓርላሜንት የውጭ ጉዳይና አውሮፓ ጉዳዮች ሊቀመንበር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 12፣ 2013 (ኤፍቢሲ) አምባሳደር ዘነቡ ታደሰ ከጣሊያን ሪፓብሊክ ፓርላሜንት የውጭ ጉዳይና አውሮፓ ጉዳዩች ሊቀመንበር ፒዬሮ ፋሲኖ ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ተወያዩ።

አምባሳደሯ በውይይቱ ወቅት በኢትዮጵያ የተካሄደውን የለውጥ ሂደትና ለውጡ በህወሓት ሴራ እንዴት እንደተፈተነ፣ ከሴራ ወደ ግልፅ ማጥቃት በመሻገር በመከላከያ ሰራዊት አባላት እና በንፁሃን ላይ ዘርን መሰረት በማድረግ ስለፈፀመው ግፍ አስረድተዋል፡፡

ይህንንም ተከትሎ ሰላማዊ ዜጎች ሳይጎዱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስለተጠናቀቀው የመንግስት የህግ ማስከበር እንቅስቃሴ እንዲሁም አሁን በትኩረት እየተሰራ ያለውን ወንጀለኞችን ለህግ የማቅረብ፣ የተፈናቀሉትን ዜጎች መልሶ የማቋቋም እና የተጎዱትን የመሰረተ ልማት ጥገና ስራ በተመለከተ ለሊቀ መንበሩ በዝርዝር አብራርተዋል።

ሊቀመንበሩ በበኩላቸው የህወሓት ወንጀለኛ ቡድን ለህግ ማቅረብና ተገቢውን ውሳኔ እንዲያገኙ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ፤ ለተፈናቀሉት ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ የማቅረብ እና በሂደትም መልሶ ማቋቋም አስፈላጊ እንደሆነ ለዚህም ጣሊያን አስፈላጊውን ሁሉ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ የሚፈጠር ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በቀጣናው ምን ሊያመጣ እንደሚችል እንደሚገነዘቡ እና ለኢትዮጵያ ሰላም አጥብቀው እንደሚሰሩ ከኤርትራ ጋር ያለው የሰላም ግንኙነት ተጠናከሮ መቀጠል እንዳለበት፣ ኢትዮጵያ በቀጠናው የምትጫወተውን የሰላም ማስከበር ሚና አጠናክራ እንድትቀጥል ፈላጎታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እያካሄዱ ያለውን ለውጥ እንደሚደግፉ፣ በጋራ ጉዳዮች፣ በኢንቨስትመንት፣ በህዝብ ለህዝብ፣ በባህል፣ ቱሪዝምና በኢኮኖሚ ትብብር ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር እንደሚፈልጉ አንስተዋል።

በተጨማሪም ሊቀመንበሩ የሚመሩት የጣሊያን ፓርላማ የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ከኢትዮጵያ አቻው ጋር የልምድ ልውውጥ ማድረግ እና በቅርበት መስራት እንደሚፈልጉ መግለጻቸውን በሮም ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.