Fana: At a Speed of Life!

በጋራ ድንበር አካባቢ በሱዳን በኩል የተደረጉ አዳዲስ ለውጦች እና እንቅስቃሴዎች የቀደሙ ስምምነቶችን የሚጥሱ በመሆናቸው በአስቸኳይ እንዲቆሙ ኢትዮጵያ አሳሰበች

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 14 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁለተኛው የኢትዮ ሱዳን የድንበር ጉዳዮች ከፍተኛ ደረጃ የፖለቲካ ውይይት ተጠናቀቀ፡፡
ውይይቱ በሱዳን ካርቱም ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየ ሲሆን በዛሬው እለት ተጠናቋል፡፡

በዚህ ወቅትም ሁለቱ ወገኖች በጋራ የድንበር አካባቢ ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ሃሳብ የተለዋወጡ ሲሆን፥ ከጥቅምት ወር መጨረሻ ጀምሮ በጋራ ድንበር አካባቢ በሱዳን በኩል የተደረጉ አዳዲስ ለውጦች እና እንቅስቃሴዎች የቀደሙ ስምምነቶችን የሚጥሱ መሆናቸው ተነስቷል፡፡

ከዚህ ባለፈም መሬት ላይ ያለውን እውነታ የሚለውጡ በመሆናቸው በአስቸኳይ እንዲቆሙና ወደቀደመ ቦታቸው እንዲመለሱ ኢትዮጵያ አሳስባለች፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በገበሬዎች እና ባለሃብቶች ንብረት ላይ የደረሰው ከፍተኛ ጉዳት እና የዜጎች መፈናቀል ትኩረት እንደሚያሻውና በአስቸኳይ መታረም እንዳለበትም ነው ያሳሰበችው፡፡

በተጨማሪም የሁለቱ ሃገራት የጋራ ድንበርን በተመለከተ ያሉ ማናቸውም አይነት ልዩነቶች ሁሉንም በሚያስማማ መንገድ በውይይት ስለ መፍታትና የወደፊት አቅጣጫ ምን ይሁን በሚለው ዙሪያም በሁለቱ ቀናት ውይይት መክረዋል፡፡

በኢትዮጵያ በኩል የድንበሩን ጉዳይ ሰላማዊ በሆነ መልኩ ከቀደሙት ስምምነቶች ጋር በተጣጣመ መንገድ ከድንበሩ ጋር በተያያዘ የተቋቋሙና ስራቸውን ያላጠናቀቁ ልዩ ልዩ ኮሚቴዎች ስራቸውን እንደገና እንዲጀምሩ በማድረግ መፈታት እንዳለበት ተገልጿል፡፡

ይህም የሁለቱን ሃገራት ስትራቴጂካዊና ወንድማማቻዊ ግንኙነት እንዲሁም የሁለቱን ህዝቦች ፍላጎትና ጥቅም የሚያስጠብቅ እንደሚሆንም ነው የተገለጸው፡፡

ሁለቱ ወገኖች ቀጣይ ምክክራቸውን በሚመች ጊዜ በአዲስ አበባ ለማካሄድ እና ለመሪዎቻቸው የዚህን ስብሰባ ሂደት እና ውጤት ሪፖርት በማቅረብ በሚሰጣቸው አቅጣጫ መሰረት ምክክራቸውን ለመቀጠል በመስማማት ስብሰባቸውን አጠናቀዋል፡፡

በቀጣይ ስብሰባ በአካባቢው ያሉ ለውጦችን በመገምገም የድንበር ኮሚቴዎች ስራቸውን በሚቀጥሉበት ሁኔታ ላይ እንደሚመክሩም ይጠበቃል፡፡

በኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራ ልዑክ ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ጋር በሱዳን ቆይታው ውይይት አድርጓል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.