ሀገራዊ ለውጥ ያላስደሰታቸው አካላት በህዝበ ሙስሊሙ ላይ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በማድረስ ላይ ናቸው-የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዩች ጠቅላይ ምክር ቤት
አዲስ አበባ፣ታህሳስ 24፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) ሀገራዊ ለውጥ ያላስደሰታቸው እና የህዝበ ሙስሊሙን አንድነት እና ለሀገሩ የሚያበረክተው ከፍተኛ እገዛ የማይዋጥላቸው አካላት በህዝበ ሙስሊሙ ላይ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በማድረስ ላይ መሆናቸውን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዩች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ።
በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ የሰጠው ምክር ቤቱ፥ ኢትዮጵያዊያን መስሊሞች ከጥንት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ለሀገሪቱ እድገት እና ሰላም በተሰማሩበት መስክ ከፍተኛ እገዛ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አመልክቷል።
በተለያዩ ጊዜያትም በቀጥታም ሆነ በተዘዋወሪ መብታቸው ሲጣስና በግልም ሆነ በጋራ አቅሙ በሚፈቅደው መጠን መብቱ ለማስጠበቅ በሰላማዊ መንገድ ሲታገል ቆይቷልም ነው ያለው።
በአሁኑ ሰዓት ለመጣው ሀገራዊ ለውጥ ከፍተኛ እገዛ አድርገዋል ።
ከዚህ ሀገራዊ ለውጥ መምጣትጋር ተያይዞ መንግስት የህዝበ ሙስሊሙ አንድነት የሚጠናከርበት እና የመጅሊስ አወቃቀር የሚስተካከልበት መንገድ ለማመቻቸት ላደረገው አስተዋጽኦ ምስጋናውምን ያቀርባል ብሏል በመግለጫው።
ነገር ግን ይህ ሀገራዊ ለውጥ ያላስደሰታቸው እና የህዝበ ሙስሊሙን አንድነት እና ለሀገሩ የሚያበረክተው ከፍተኛ እገዛ የማይዋጥላቸው አካላት በህዝበ ሙስሊሙ ላይ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በማድረስ የሀገሪቱን ሰላም እና የህዝቦች አብሮነትን የሚፃረር ተግባር በማከናወን ላይ መሆኑን አንስቷል።
ጠቅላይ ምክር ቤቱ በተለያዩ አካባቢዎች በህዝበ ሙስሊሙ ላይ የሚደርሱትን ችግሮች አስመልክቶ ባደረኩት የዳሰሳ ጥናት ችግሮቹ አስከፊ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን አውቂያለሁ ብሏል።
በሀይማኖታቸው ምክንያት የህይወት መጥፋት፣ የአካል መጉደል፣ ሀብት እና ንብረት ጥሎ ለስደት መዳረግ፣ የመስጂድ ማፍረስ እና ቃጠሎ ፣ የንግድ እና የመኖሪያ ቤቶች ዘረፋ፣ ቃጠሎ እና ውድመት፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ እና በተለይ በክልሎቹ ሚዲያ ፍትሀዊነት የጎደለው መረጃ ለህዝቡ ማሰራጨት እና ስለሙስሊሙ ችግር ተገቢውን መረጃ በወቅቱ አለማድረስ የሚሉትን ችግሮች ምክር ቤቱ በመግለጫው ጠቁሟል።
በተጨማሪም የመስገጃ ቦታ እጦት እና በትውልድ ቀዬው መቀበር አለመቻል፣ ምንም እንኳን ሙስሊም የሚገለገልባቸው አብዛኞቹ መስጂዶች በግዢና እና በስጦታ የተገኙ ቢሆኑም እነዚህን እና በምሪት የተገኙ ጥቂት ቦታዎች ላይ ተደጋጋሚ የይዞታ ማካለል እና የግንባታ ፈቃድ የመስጠት ችግር በመቀበሪያ ቦታ እጦት ለከፋ እንግልት መዳረግ ናቸው ሲል ጠቅላይ ምክር ቤቱ ገልጿል።
የጠቅላይ ምክር ቤቱ እነዚህ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተደጋጋሚ የሚከሰቱ የመብት ጥሰቶች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በሰከነ መንገድ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካለት በተዋረድ በተደጋጋሚ እያቀረበ እንደሚገኝም ነው ያመለከተው።
ሆኖም ችግሮቹ እየተባባሱ ለመምጣታቸው ማሳያ በቅርቡ በአማራ ክልላዊ መንግስት በምስራቅ ጉጃም ዞን በሞጣ ከተማ በሙስሊሞች ላይ የደረሰው ጥቃት አንዱ ነው ብሏል ጠቅላይ ምክር ቤቱ፡፡
በእስካሁንም በጥቃቱ ተሳታፊ ናቸው የተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ ላይ መሆኑን በመልካም ጅማሮ ተመልክቶታል።
ሆኖም ይቅርታ መጠየቅ፣ ተገቢውን ካሳና መልሶ ግንባታ እንዲሁም የደህንነት ዋስትና መስጠት ከቃል የዘለለ የጽሁፍ እና የተግባር ይፋዊ ምላሽ እንዲሰጥ የክልሉን መስተዳድር ጠይቋል።
የፌደራል መንግስትና የሚመለከታቸው ተቋማትም የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች መሰረታዊ ጥያቄዎች በሆኑት የሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እና የችግሮቹን አሳሰቢነት ከግምት ውጥ በማስገባት የህግ የበላይነት ለማስከበር የሀገራቸን ህገ መንግስት በሚያዘው መሰረት ጣልቃ በመግባት በአፋጣኝ የማያዳግም መፍትሄ ይስጠን ሲል ጠይቋል።