የሀገር ውስጥ ዜና

የምጣኔ ሃብት ዘርፉን ለማስፋት ኢትዮጵያ ከብራዚል ጋር እንደምትሰራ ተገለጸ

By Meseret Awoke

December 24, 2020

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 15፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የምጣኔ ሃብት ዘርፉን ለማስፋት ኢትዮጵያ ከብራዚል ጋር በትብብር እንደምትሰራ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ገለጹ ፡፡

ሰብሳቢው በኢትዮጵያ ከብራዚል አምባሳደር አቪ ፔድሮሶ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት የረጅም ጊዜ ዴፕሎማሲያዊ ታሪክ እንዳላቸውና የሁለትዮሽ ግንኙነቱን የበለጠ ለማጠናከር የፓርላማ የወዳጅነት ቡድን ለመመስረት እንደሚሰራ ጠቅሰው ወዳጅነቱ ፍሬያማና ውጤታማ እንዲሆን የምጣኔ ሃብትን በማስፋት፣ በፓርላሜንታዊ እና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ታግዞ እንደሚቀጥል ነው የገለጹት ፡፡

ዶክተር ነገሪ በትግራይ ክልል የተከናወነውን የሕግ ማስከበር እርምጃ አስመልክተው ለአምባሳደር ፔድሮሶ ያብራሩላቸው ሲሆን፣ አምባገነኑ የሕወሓት ቡድን ላይ የተወሰደው እርምጃ እንደተጠናቀቀና በክልሉ ሰላም መስፈን እንደቻለ ተናግረዋል፡፡

በሕግ ማስከበር እርምጃው ከቀያቸው ተፈናቅለው ለነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች መንግስት አስፈላጊውን የሰብዓዊ እርዳታ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ ቡድኑ ያፈራረሳቸውን መሰረተ-ልማቶች ወደነበሩበት የመመለስ ስራ እየሰራ መሆኑንም ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡

የብራዚል ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ እንዲሰማሩም ጠይቀዋል፡፡

አምባሳደር ፔድሮሶ በበኩላቸው የምጣኔ ሃብት ዘርፉን ለማስፋት ብራዚል በግብርናው፣ በኢንቨስትመንት፣ በንግድና ቴክኖሎጂ ሽግግር ከኢትዮጵያ ጋር እንደምትሰራ ጠቅሰዋል፡፡

አምባሳደሩ ጨምረውም የሃገራቸው ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ እንዲሰማሩ ለማድረግ እንደሚሰሩ መናገራቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!