Fana: At a Speed of Life!

ፖለቲካ ፓርቲዎች በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 15፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ ከወዲሁ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እያከናወኑ መሆኑን ፖለቲካ ፓርቲዎች አስታወቁ።

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ /አብን/፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ እና የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ትዴፓ/ አመራሮች ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

ፓርቲዎቹ በቀጣዩ ምርጫ ተወዳዳሪ እና ተመራጭ ለመሆን ለህዝብ ይበጃል ያሉትን ፖሊሲ ከመቅረጽ ባለፈ ምርጫው ሰላማዊ፣ ተዓማኒ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ የበኩላቸውን ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸው ገልጸዋል፡፡

የሀገራዊ ምርጫው ተዋናይ የሆኑት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ገዥው ፓርቲ እና የምርጫ ቦርድ በምርጫ ሂደቱ ላይ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በሚገባ መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የአብን ምክትል ሊቀመንበር አቶ የሱፍ ኢብራሂም ፓርቲያቸው ለስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰፊ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው የምርጫ ስትራቴጂዎችን ዝግጅት እያጠናቀቀ እንደሚገኝ እንዲሁም አባላት እና እጩዎችን በመመልመል እያሰለጠነ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

የኢዜማ የምርጫ ስትራቴጂ እና ማኔጅመንት ኮሚቴ ጸሃፊ ወይዘሮ ከውሰር እድሪስ በበኩላቸው፣ ፓርቲያቸው ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት ስልጠና በመስጠት እጩዎች የሚተዳደሩበት የምርጫ ስነ ምግባር ሰነድ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

ማህበራዊ ፍትህ የኢዜማ ፍልስፍና መሆኑን የሚናገሩት ወይዘሮ ካውሰር፦ ከዚህ ፅንስ ሃሳብ የሚመነጩ እና ለማህበረሰቡ ሰፊ ፋይዳ ያላቸው የተለያዩ ፖሊሲዎች መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል፡፡

የትዴፓ ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርኸ ደግሞ በቀጣዩ ምርጫ ለመሳተፍ ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ በቅርቡ በትግራይ ክልል የተከሰተው ሁኔታ ተግዳሮት እንደሆነባቸው አንስተዋል፡፡

ሆኖም ማህበረሰቡን ቅድሚያ የሚሰጥ በድህነት ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን የሚያበረታታ ፖሊሲ በመቅረጽ እየተንቀሳቀሱ ስለመሆኑ ያነሳሉ፡፡

አመራሮቹ ምርጫ ሰላማዊ፣ ተዓማኒ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲካሄድ በሂደቱ የሚሳተፉ አካላት የበኩላቸው ሚና መጫዎት እንዳለባቸው አንስተዋል፡

በዚህ ረገድ አሁን ላይ በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ እና ፖለቲካ ለመስራት አስቸጋሪ የሆኑ ፅንፈኛ ኃይሎችን በጋራ መዋጋት ይገባል የሚሉት አቶ የሱፍ እና ወይዘሮ ካውሰር ከግለሰቦች እና ቡድኖች አስተሳሰብ ባለፈ የትኛውም ፓርቲ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ተንቀሳቅሶ ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር እና አሸናፊ ሃሳብ ይዞ ሊቀርብ ይገባል ብለዋል፡፡

ዶክተር አረጋዊም በሂደቱ ላይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የምርጫ ህግን አክብሮ ከመንቀሳቀስ ባለፈ ተመሳሳይ ርዕዮተ ዓለም ያለው ጥምረት በመፍጠር አሸንፎ የሚወጣ ሃሳብ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው አውስተዋል፡፡

ከምርጫ ቦርድ ጋር በተያያዘ አቶ የሱፍ አሁን ላይ ቦርዱ የተሻለ ሪፎርም ማካሄዱን ጠቁመው ምርጫውን በሃላፊነት እና በብቃት ይወጣል ብለው እንደሚያምኑም ነው የተናገሩት፡፡

ዶክተር አረጋዊ በርኸ በበኩላቸው ምርጫ ቦርድ በተለይ ግጭት በሚከሰትባቸው ቦታዎች ላይ ወርዶ ሁኔታዎችን ለምርጫ ዝግጁ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ለዚህም እስከ ወረዳ ድርስ የምርጫ ጣቢያዎችን በማቋቋም ገለልተኛ አባላትን መመደብ እንዳለበት ነው ያሳሰቡት፡፡

 

በመላኩ ገድፍ

 

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.