የሀገር ውስጥ ዜና

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ውይይት እያካሄደ ነው

By Meseret Demissu

December 25, 2020

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 16 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በመቀሌ ከተማ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ፣ የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ዶክተር አብርሃም በላይ፣ የሰሜን ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል በላይ ስዩም እና የመቀሌ ከተማ ጊዜያዊ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አታክልቲ ሃይለስላሴ ውይይቱን እየመሩ ይገኛል።

በውይይቱም የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተወጣጡ በርካታ ነዋሪዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ተሣታፊዎቹ በውይይታቸው የሕወሓት ጁንታ የአገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ያደረሰውን ጥቃት አውግዘዋል።

በክልሉ የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደርም መዋቅሩን እስከታችኛው የአስተዳደር እርከን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

ነዋሪዎቹ የመቀሌን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅም ህዝባዊ ፖሊሶች በአስቸኳይ ተደራጅተው በከተማው ስራ እንዲጀምሩ ጠይቀዋል።

መንግስት የኤሌክትሪክ አገልግሎት እና ሌሎች የመሠረተ ልማቶች በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገቡ እንዳደረገ ሁሉ የኢንተርኔት አገልግሎትም ስራ ቢጀምር የተሻለ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በውይይቱ ማጠቃላያ ላይ ነዋሪዎቹ ላነሷቸው ጥያቄዎች በመድረኩ ላይ በተገኙት አመራሮች ምላሽና ማብራሪያ እንደሚሠጥ ኢዜአ ዘግቧል።