የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ከ157 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ

By Meseret Demissu

December 25, 2020

አዲስ አበባ ፣ታህሳስ 16 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ከ157 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡

ኢንተርፕራይዙ ቀልጣፋና ዘመናዊ በሆነ መልኩ የተጠቃሚዎቹን ፍላጎት ለማሟላት የተለያዩ ተግባራት ሲያከናውን መቆየቱም ነው የተነገረው፡፡

በበጀት ዓመቱ በአዲስ- አዳማ እና በድሬዳዋ- ደወሌ የክፍያ መንገዶች 4 ሚሊየን 1 ሺህ 31 የትራፊክ ፍሰት ለማስተናገድ ታቅዶ 3 ሚሊየን 596 ሺህ 852 ማከናወን የተቻለ ሲሆን በዚህ  ክንውኑም 90 በመቶ ሆኖ መመዝገቡ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም ከክፍያ መንገድ አገልግሎት 161 ሚሊየን 716 ሺህ 939 ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 147 ሚሊየን 55 ሺህ 754 ብር ተሰብስቧል፡፡

እንዲሁም ከልዩ ልዩ ገቢዎች (ከማስታወቂያ ቦታዎች ኪራይ፣ ከወደሙ የመንገድ ሃብቶች ካሳ ክፍያ፣ ከተሽከርካሪ ማንሻና መጎተቻ…) 10 ሚሊየን 388 ሺህ 161 ብር ገቢ ሲገኝ በአጠቃላይ 157 ሚሊየን 443 ሺህ 915 ብር መሰብሰብ መቻሉን ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡