Fana: At a Speed of Life!

የወንጀል ሕግ ስነ ስርዓትና የማስረጃ ሕግ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን መሰረት ባደረገ መልኩ ይሻሻላል – የሕግ ባለሙያዎች ማህበር

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 17 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የወንጀል ሕግ ስነ ስርዓትና የማስረጃ ሕግ፤ ሕገ መንግስቱን መሰረት ያደረገና አገሪቷ የፈረመቻቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ባካተተ መልኩ የሚሻሻል መሆኑን የሕግ ባለሙያዎች ማህበር ገለጸ።
ላለፉት 60 ዓመታት ሥራ ላይ የቆየው የወንጀል ሕግ ስነ ስርዓትና የማስረጃ ሕግ ረቂቅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ የፍትህና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እየታየ ይገኛል።
የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማሕበር በረቂቁ ላይ የተለያዩ የዘርፉ ሙያተኞችን በማሳተፍ በአዲስ አበባ ውይይት እያካሄደ ይገኛል።
የማሕበሩ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ ጌታቸው በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ ሕጉ ረጅም ዓመት ያስቆጠረ በመሆኑ ዘመኑን የዋጀ አይደለም።
በተለይም በየዘመናቱ ወንጀሎች እየረቀቁ በመምጣታቸው ወንጀሎችን በቅጡ ለመዳኘት በተለያየ መልክ የወጡትን ሕጎች መጠቀም ግድ ነው ብለዋል።
የሽብር ወንጀሎችን እንዲሁም ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ህገ ወጥ ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ የማቅረብ ወንጀሎችን ለመዳኘት ‘እዚህም እዚያም’ ያሉ ሕጎችን መዳሰስ አስፈላጊ እንደነበረ በማሳያነት ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም የቀደመው ሕግ የፍርድ ክለሳ የሚደረግበትን ሁኔታ የማይፈጥር መሆኑን ነው የገለጹት።
ከዚህ በፊት አንድ ግለሰብ “ሰው ገድለሃል ተብሎ ዕድሜ ልክ ተፈርዶበት ከአምስት ዓመት በኋላ ሟች አልሞትኩም” ያለበት ሂደት አጋጥሞ ሁኔታውን ለማረም የሚያስችል የህግ አግባብ እንዳልነበር አስታውሰዋል።
የረቂቅ ሕጉ አማካሪ ጉባኤ አባል አቶ ቸርነት ሆርዶፋ ረቂቁ ሕገ መንግስቱን መሰረት አድርጎ እንዲሻሻል መደረጉን ጠቅሰዋል።
ሕገ መንግስቱን ማክበር፣ አገሪቷ የፈረመቻቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ማካተትና መሰረታዊ የሆነ የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ፍልስፍናን ያካተተ መሆን እንዳለበትም ነው የጠቆሙት።
ከዚህ ጎን ለጎን በመንግስት ወንጀል የመከላከል ፍላጎትና በዜጎች መሰረታዊ መብት ማስከበር መካከል ያለውን ሚዛን በጠበቀ መልኩ ሊሻሻል እንደሚገባም አስረድተዋል።
ሌላው የአማካሪ ጉባኤው አባል አቶ ያለለት ተሾመ ደግሞ ረቂቅ ሕጉ አሁንም ክፍተቶች እንዳሉበት አውስተው፤ አንድ ሕግ ሲወጣ መሰረታዊ መርሆዎችን መሰረት አድርጎ መሆኑን ጠቅሰዋል።
‘ሕጉ ከተረቀቀ በኋላ የትርጉም ችግር እንዳያመጣ ሁሉም እንዲረዳው ሆኖ መዘጋጀት አለበትም ብለዋል።
ረቂቅ ሕጉ መግባባት የተደረሰበት፣ ግልፅ፣ በቀላሉ መረዳት የሚቻል፣ ከሌሎች ሕጎች ጋር የተገናዘበ መሆን እንዳለበትም ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በሙያ ማሕበሩ አማካኝነት የሚነሱትን አስትያየቶች እንዲካተቱ ጥረት እንደሚያደርግ ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ተስፋዬ ዳባ ገልጸዋል።
መሰል አስትያየቶች እንዲቀርቡና እንዲካተቱ ለማድረግ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር በመነጋገር ረቂቁ የሚጸድቅበት ቀን እንዲራዘም መደረጉንም ጠቁመዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.