ሀገር አቀፍ ብሔራዊ የሴቶች የሰላም ምክር ቤት ተቋቋመ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 24፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሀገር አቀፍ ብሔራዊ የሴቶች የሰላም ምክር ቤት መቋቋሙን የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሰላም ሚኒስቴር ከጀስቲስ ፎር ኦል እና ከኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ባዘጋጀው መድረክ ላይ የምክር ቤቱን መቋቋም ይፋ አድርጓል።
የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ አልማዝ መኮንን ብሔራዊ የሴቶች የሰላም ምክር ቤት መቋቋም ሴቶችና የሰላም እናቶች አደረጃጀታቸውን በማጠናከር ጥምረት እንዲፈጥሩ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።
በየአካባቢው የሚታዩ ግጭቶችን፣ ሁከቶችንና ደም መፋሰስን አስቀድሞ ለመረዳትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ በመሆን ለመፍታት ሴቶች ሚናቸውን እንዲወጡ ማስቻልም የምክር ቤቱ አላማ መሆኑም ተናግሯል።
ምክር ቤቱ በ2012 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ እና ከዚህ ጋር ተያይዞ ሊመጡ የሚችሉ የሰላም ስጋቶችን ቀድሞ ለመከላከል እንደሚሰራ ተገልጿል።
ምክር ቤቱ በየአካባቢው ያሉ ወቅታዊ የሰላምና የፀጥታ ችግሮችን በመለየት ሪፖርት ማድረግና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሰባሰብ የትምህርትና የንቃተ ህሊና ስራዎችን ይሰራልም ነው የተባለው።
ከሰላም እናቶችና ከሰላም አምባሳደሮች ጋር በጥምረት የተቋቋመው ምክር ቤት ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ 55 ተፅዕኖ ፈጣሪ የሴት አባላትን ያቀፈና 11 ስራ አስፈፃሚ አባላት ያሉት ነው።
አባላቱ በየዓመት ሁለት ጊዜ አስራ አንዱ ስራ አስፈፃሚ አባላት ደግሞ በዓመት አራት ጊዜ የውይይት መድረክ እንደሚኖራቸው ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።