Fana: At a Speed of Life!

የታሪክ ምሑራንና ፀሐፊያን በአገር ግንባታና በብሔራዊ መግባባት ላይ የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ማህበራቸውን ዳግም መሰረቱ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 20 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአገር ግንባታና በብሔራዊ መግባባት ላይ የሚጠበቅባቸውን ሚና ሙያዊ ስነ-ምግባርን በተላበሰ መልኩ ለመወጣት ማኅበራቸውን ዳግም ለመመስረት መስማማታቸውን የታሪክ ምሑራንና ፀሐፊያን አስታወቁ።
ታሪክ ምሑራንና ፀሐፊያኑ ይህን ያስታወቁት ለአራት ቀናት በቢሾፍቱ ያካሄዱትን የምክክር መድረክ ማጠቃለያ አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ነው።
የምክክር መድረኩ በሠላም ሚኒስቴር አስተባባሪነት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር እየተካሄደ የሚገኘው የብሔራዊ የማኅበረሰብ ተኮር የምክክር መድረክ አካል ነው።
የታሪክ ምሑራንና ፀሐፊያኑ ከምክክራቸው በኋላ ‘የታሪክ ባለሙያዎች የቢሾፍቱ ስምምነት 2013’ በሚል ባለ አራት ነጥብ የጋራ ስምምነት አውጥተዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪና የኮሚቴው አባል ወይዘሮ ጽጌረዳ ወልደብርሃን “እንደ ዕውቀት ማኅበረሰብ ተቀራርበን ለመስራት ተስማምተናል” ያሉባቸውን ነጥቦች አብራርተዋል።
በየታሪክ ሙያ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመጡበትን ጫናና ተፅዕኖዎች በመቋቋም በሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች የተሳሳቱ የታሪክ ትርክቶችን ለማረምና በአሳማኝ የታሪክ ማስረጃዎች ላይ የተመሰረቱ ሕትመቶችን ለማውጣት ስምምነት መድረሳቸውን አስታውቀዋል።
ለዚህም ተቋርጦ የቆየውን የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር ዳግም በመመስረት ማንቀሳቀስ አንደኛው እርምጃ መሆኑ በመግለጫው ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል “በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስተባባሪነት ተዘጋጅቶና ተተችቶ በየካቲት 2012 ዓ.ም የፀደቀው የኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ ታሪክ የትምህርት ኮርስ ተግባራዊ ያልሆነበትን ምክንያት ተቋሙን በመጠየቅ የተዘጋጀው ሞጁል ለዩኒቨርሲቲዎች እንዲሰራጭና ትምህርቱ የሚጀመርበት ሁኔታ እንዲመቻች እንሰራለን” ብለዋል።
ምሑራኑና ፀሐፊያኑ “በታሪክ ትምህርትና በፖለቲካ መካከል ያለውን ጤናማ ትስስር ለማዳበር፣ ፖለቲከኞች በታሪክ ትምህርት ላይ የሚያሳድሩትን ጤናማ ያልሆነ ጫና ለማስተካከልና ችግሩን በሂደት ለመፍታት ተከታታይ ውይይት እናካሂዳለን” ብለዋል ።
ከዚህ ቀደም የተሰሩ ስራዎችን ለማጠናከርና በምክክር መድረኩ ስምምነት የተደረሰባቸውን ውሳኔዎች ተፈጻሚ ለማድረግ 12 አስተባባሪዎች ያሉት ኮሚቴ መሰየማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.