Fana: At a Speed of Life!

የጸረ ኮሌራ ክትባት ዘመቻ በምዕራብ ጉጂ ዞን አባያ ወረዳ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 21፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የጸረ ኮሌራ ክትባት ዘመቻ በምዕራብ ጉጂ ዞን አባያ ወረዳ ተጀምሯል፡፡

ክትባቱ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ፣ የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ደረጀ አብደና እና ሌሎች ሃላፊዎች እንዲሁም የወረዳው ነዋሪዎች በተገኙበት ነው የተጀመረው።

በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱም አቶ አስቻለው ክትባቱ በሚሰጥበት ወቅት የሕክምና ባለሙያዎች እና ተከታቢዎች ራሳቸውን እና ማሕበረሰቡን ከኮቪድ-19 በሽታ ለመከላከል የመከላከያ መንገዶችን መከተል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

አቶ አስቻለው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ወረርሽኙ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በስተቀር በሁሉም ክልሎች መከሰቱን ተናግረዋል።

የኮሌራ ወረርሽኝ በተከሰተባቸው ቦታዎች ላይ 15 ሺህ 623 ሰዎች በበሽታው ሲያዙ 275 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡

ወረርሽኙ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ክልል 5 ዞኖች 18 ወረዳዎች ላይ፣ በሲዳማ ክልል 8 ወረዳዎችና በጋምቤላ ክልል አንድ ወረዳ ወረርሽኙ እንዳለ ታውቋል ብለዋል።

በዚህ ዓመትም ማለትም ከሐምሌ 2012 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ወረርሽኙ 2 ሺህ 333 የኮሌራ ኬዝ እና 44 ሞት የተከሰተ ሲሆን በአጠቃላይ ከ2011 ጀምሮ ደግሞ አስከአሁን ድረስ 17 ሺህ 956 ሰዎች የታመሙ ሲሆን 319 ሰዎች በኮሌራ በሽታ ሕይወታቸው አልፏል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከክልሎች እና ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የኮሌራ በሽታ ቅኝት በማከናወንና ለወረርሽኙ ፈጣን ምላሽ እየሰጠ እንደሚገኝ ተነግሯል።

ባለፈው ዓመት የኮሌራ ክትባት በኦሮሚያ 5 ወረዳዎች፣ በደቡብ 5 ወረዳዎች፣ በሱማሌ 3 ወረዳዎች እና በአፋር 2 ወረዳዎች እንዲሁም በአዲስ አበባ በተመረጡ ቦታዎች ላይ በ2012 የመጀመሪያ ዙር ለ613 ሺህ 572 ተጋላጭ ሰዎች የኮሌራ ክትባት እንደተሰጣቸው መናገራቸውን ኢንስቲትዩት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በምዕራብ ሀረርጌ ዞን አምስት ወረዳዎች ላይ ሁለተኛ ዙር 285 ሺህ 354 ሰዎች ክትባቱን አግኝተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.