Fana: At a Speed of Life!

እየተፈጸሙ ያሉ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ለማስቆም መንግስት በለውጥ ሀይል ስም የተሰገሰጉ አመራሮቹን ማጥራት አለበት -የህግ ባለሙያዎች

አዲስ አበባ ፣ታህሳስ 22 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ እየተፈጸሙ ያሉ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለማስቆም መንግስት በለውጥ ሀይል ስም የተሰገሰጉ አመራሮቹን ማጥራት እንዳለበት የህግ ባለሙያዎች ገለጹ።
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የህግ ባለሙያዎቹ÷ ህጋዊ መሰረቱን እየለቀቀ ያለው የፌደራል እና የክልል መንግስታት ግንኙነትም ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ መሆኑን ነው ያነሱት።
ለዚህም የፌደራል መንግስቱ በክልሎች ጣልቃ የሚገባበት ህጋዊ አካሄድ መኖሩን የሚያነሱት የህግ ባለሙያዎች÷ የፌደራሉ መንግስት የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አውስተዋል፡፡
መንግስት በተለያዩ ክልሎች የበርካታ ንፁሃንን ህይወት ለቀጠፉ እና ሺህዎችን ከመኖሪያ ቀያቸው ያፈናቀሉ ጥቃቶችን የመሩ እና ያስተባበሩ አመራሮችን በፍጥነት በቁጥጥር ስር አውሎ ተጠያቂ እንዲያደርጋቸውም ጠይቀዋል።
የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህሩ ዶክተር ማርሸት ታደሰ÷ ሀገሪቱ በአፈሙዝ ብቻ ህግ የምታስከብርበት ሳይሆን የሽግግር ጊዜ ላይ መሆናችን ሊዘነጋ አይገባም ይላሉ፡፡
ነገር ግን የሽግግር ሂደቱን የሚያጓትቱ አካሄዶች ቸል ሊባሉ እንደማይገባ ጠቁመው÷ በሀገሪቱ ባለፉት ሁለት አመት ተኩል ለተከሰቱ ግጭቶች እና ማንነትን መሰረት ያደረጉ ዘግናኝ ጥቃቶች መነሻቸው ህዝብ እንዳልሆነ ይታወቃልም ነው ያሉት።
መንግስትም ለጥቃቶቹ ከስልጣን የተወገደውን ፅንፈኛ ቡድን እና ርዝራዦቹን እንዲሁም የለውጥ ሀይሉ ውስጥ የተቀላቀሉ ግን ደግሞ ምንም አይነት የለውጥ ፍላጎት የሌላቸውን አመራሮች ተጠያቂ ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል።
በተወሰኑት ላይም ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን ጠቁመው÷ህዝብን ከህዝብ እያጋጩ የንፁሃንን ደም ማፍሰስ የቀጠሉ አመራሮች ግን አሁንም ስራ ላይ ስለመሆናቸው ይጠቅሳሉ።
አያይዘውም የበግ ለምድ ለብሰው የለውጥ ሀይል የሚመስሉ አካላት ተጠያቂነት ጊዜ ሊሰጠው አይገባም ብለዋል።
የህግ ባለሙያውና የፀረ ሙስና ተሟጋቹ ክብረአብ አበራ በበኩላቸው ÷መንግስት በውስጡ ለተሰገሰጉ አመራሮች የበዛ ትዕግስት ያሳየው ለውጡ ሁሉንም አፍርሶ ከዜሮ የሚነሳ አይደለም በሚል እያሻሻለ መሄድን በመምረጡ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም ህግ የማስከበር አቅሙን ለማጠናከር የፍትህ እና ፀጥታ ተቋማትን ሪፎርም ለማድረግ ሰፊ ትኩረት አድርጎ መስራቱን አንስተዋል።
ከለውጥ አመራሩ ጋር የሚሰሩ እና ጥፋት ውስጥ ያሉ አመራሮችም እንዲታረሙ ከፍ ያለ ጥፋት ሲፈፅሙም ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው እያደረገ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።
ዶክተር ማርሸት ግን አሁን ላይ በአመራርነት ላይ ያሉት ብቻ ሳይሆን የቀድሞዎቹም ተጠያቂነታቸው ሊረጋገጥ ይገባል ባይ ናቸው።
በመንግስት በኩል እየተካሄዱ ያሉ የሪፎርም ስራዎችን አድንቀው÷ የሚታዩ መዘግየቶች እየተፈፀሙ ካሉ ተደጋጋሚ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አንፃር ጥያቄ የሚያስነሱ በመሆናቸው ሊታሰብባቸው ይገባልም ነው የሚሉት።
በፋሲካው ታደሰ
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.