Fana: At a Speed of Life!

ብ/ጄ ኪዱ አለሙ ኬንያ ሆነው ለተለያዩ ሀገራት የመከላከያ ሀይሎች የሀገሪቱን ሚስጢሮች አሳልፈው ሲሰጡ እንደነበር ፖሊስ ገለጸ

አዲስ አበባ ፣ታህሳስ 22 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)ብርጋዴል ጀነራልኪዱ አለሙ ኬንያ ሆነው ለተለያዩ ሀገራት የመከላከያ ሀይሎች የሀገሪቱን ሚስጢሮች አሳልፈው ሲሰጡ እንደነበር ፖሊስ ገለጸ።
መርማሪ ፖሊስ ይህንን የገለጸው ተጠርጣሪው ዛሬ ለሶስተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት ነው።
ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው 13 ቀን ውስጥ በርካታ የምርመራ ስራ መስራቱን አብራርቷል።
በዚህም ኬንያ ሆነው ለተለያዩ ሀገራት የመከላከያ ሀይሎች የሀገሪቱን ሚስጢሮች አሳልፈው ሲሰጡ እንደነበርና ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ሲፈጸም ለጸረ ሰላም ሀይሉ በሳተላይት በመጠቀም ወታደራዊ አመራርነትና ድጋፍ ሲሰጡ እንደነበር ገልጿል።
በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊትን የሚያመላክቱ የጉዳት መጠን ማስረጃዎችን ማምጣቱንም ለችሎቱ አስረድቷል።
የምርመራ መዝገቡንም በሰውና በሰነድ ማስረጃ አጠናክሮ ለሚመለከተው አካል ለመስጠት ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ጠቁሟል።
የተጠርጣሪ ከጠበቃቸው ጋር ተወክለው የተገኙ ሲሆን÷ በኬኒያ አንድ ዓመት ከስምንት ወር በስራ ላይ በነበሩበት ወቅት አንድም ቀን ከኤምባሲው ወጥተው እንደማያውቁ አስረድተዋል።
በመርማሪ ፖሊስ የቀረበው የተጨማሪ ጌዜ መጠየቂያ ምክንያቶች ተገቢ አይደሉም ሲሉ ተከራክረዋል።
የአስም በሽተኛ መሆናቸውን በመጥቀስም ያለአግባብ ነው የታሰርኩት ሲሉም ተቃውመዋል።
የሁለቱን ክርክር ያዳመጠው የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎትም ለቀሪ ምርመራ ማከናወኛ 11 ተጨማሪ ቀናት ለፖሊስ ፈቅዷል።
ውጤቱን ለመጠበቅ ለጥር 3 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በቀጠሮ ቀንም መዝገቡ እንዲቀርብ አዟል።
በታሪክ አዱኛ
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.