የሀገር ውስጥ ዜና

“ምክንያታዊ ወጣትን መፍጠር” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሀገር አቀፍ መድረክ ሊካሄድ ነው

By Tibebu Kebede

December 31, 2020

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 22 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) “ምክንያታዊ ወጣትን መፍጠር” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሀገር አቀፍ መድረክ የፊታችን ቅዳሜ ይጀመራል።

መድረኩ በተለያዩ ምዕራፎች የተከፋፈለ ሲሆን ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ ከ5 ሚሊየን በላይ ወጣቶች ወጣቶች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡

እንደ ሀገር በተፈጠረው ለውጥ ውስጥ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ እንደነበር እና የለውጡን ቀጣይ ህልውና ምሉዕነት ማረጋገጥ የሚቻለው ምክንያታዊ ሆኖ በሀሳብ መሞገት የሚችል ወጣት ሲፈጠር መሆኑን መድረኩን አስመልክቶ በተሰጠ መግለጫ ተጠቅሷል።

የብልፅግና ወጣቶች ሊግ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አክሊሉ ታደሰ ከተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከሲቪክ ማህበራት ጭምር ተጋባዥ የሆኑ እንግዶች በሚዘጋጁ መድረኮች ላይ ተገኝተው ሃሳባቸውን እንደሚያካፍሉ ገልፀዋል፡፡

በተለይም ቁልፍ ለሆነው የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ እንቅስቃሴ ሀሳብ ላይ መሰረቱን አድርጎ ለውጥን ማፋፋም አቅም ያለው ወጣትን መፍጠር በዚህ ጊዜ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ እና ይህን ግንዛቤ ውስጥ ባስገባ መልኩ የሚፈጠሩ መድረኮች የተሳካ የውይይት ጊዜ ሊኖራቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሰፋ ያለውንም የምክክር ጊዜ ለወጣቶች በመስጠት በቀጣይ ለሚገነቡ ወጣት ተኮር አመርቂ ፖሊሲዎች ግብአቶች የሚገኙበት መድረክ እንዲሆንም አቅጣጫ ተቀምጧል ነው የተባለው።

መድረኩ በመላ ሃገሪቱ ከ1 ሺህ 100 በላይ ወረዳዎች፣ ዞኖች እና ከተሞች ከወጣቶች ጋር በቀጥታ ግንኙነት በማድረግ ምክንያታዊ ወጣትን መፍጠር ላይ ግብ አድርጎ እንደሚካሄድ ከብልጽግና ፓርቲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!