የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የፀረ-ሙስና ኮንቬንሽን አንቀጽ 44 ላይ የነበራትን ተዓቅቦ አነሳች

By Meseret Demissu

December 31, 2020

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 22፣ 2013( ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ወንጀለኞችን አሳልፎ መስጠት የሚደነግገው የተባበሩት መንግሥታት የፀረ-ሙስና ኮንቬንሽን አንቀጽ 44 ላይ የነበራትን ተዓቅቦ አነሳች።

የፌደራል ሥነ-ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የፀረ-ሙስና ኮንቬንሽን አንቀጽ 44 ላይ ያላትን ተዓቅቦ አንስታለች ብሏል።

ኢትዮጵያ የኮንቬንሽኑን አንቀጽ 44 አስመልክቶ ተዓቅቦ እንዳላት የኮንቬንሽኑ ምዕራፍ ሦስት ውስጥ የተመለከተውን የሙስና ወንጀልን ወንጀል አድርጎ መደንገግና ምዕራፍ አራት ዓለም አቀፍ ትብብርን አስመልክቶ በፈረንጆቹ ከ2010 እስከ 2015 ባለው ጊዜ የነበራትን አፈጻጸም ለገምጋሚ ሃገራት አቅርባ ማስገምገሟን ኮሚሽኑ ገልጿል።

የአፈጻጸም ግምገማውን ተከትሎ ኢትዮጵያ እንድታስተካክል ተሰጥተዋት ከነበሩ ምክረ ሃሳቦች አንዱ ከላይ በተጠቀሰው የኮንቬንሽኑ አንቀጽ ላይ ያላት ተዓቅቦ እንደነበር ተመልክቷል።

በዚህ ግምገማ መሠረት ኢትዮጵያ አንቀጽ 44 ላይ የነበራትን ተዓቅቦ ያነሳች ሲሆን የፕሮቶኮሉን ድንጋጌዎች በሙሉ በማክበር ግዴታዎቿን እንደምትወጣ አረጋግጣለች።

አንቀጽ 44 ላይ ያላት ተዓቅቦ መነሳቱን መቀመጫውን ኦስትሪያ ቬና ላደረገው የተባበሩት መንግሥታት የአደገኛ ዕፅ እና ወንጀል መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀችም ኢዜአ ዘግቧል።