Fana: At a Speed of Life!

በመተከል ዞን እየተወሰደ ባለው የህግ ማስከበር እርምጃ የታጠቁ ሃይሎች እጃቸውን እየሰጡ ነው

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን እየተወሰደ ባለው የህግ ማስከበር እርምጃ በርካታ የታጠቁ ሃይሎች እጃቸውን ለጸጥታ ሃይሉ እየሰጡ መሆኑን በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ኃይል አስታወቀ።
የህግ ማስከበርና የፀጥታውን ዘርፍ በበላይነት የሚመሩት ሌተናል ጀኔራል አስራት ዴኔሮ÷ የጥፋት ቡድኑ በመተከል ዞን በተለይም ቡለንና በቆጂ ወረዳዎች ዜጎችን በመግደል፣ ንብረት የመዝረፍና የማቃጠል አረመኔያዊ ተግባር መፈፀሙን አስታውሰዋል።
የተጠናከረ ዘመቻ በማካሄድ በአካባቢው ህግ በማስከበር ሰላምን ለማረጋገጥ በተደረገው ጥረት በርካታ የታጠቁ ሃይሎች እጃቸውን እየሰጡ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ታጣቂ ቡድኑ ቀደም ሲል የፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ ስጋት አድሮባቸው መኖሪያቸውን ለቀው የነበሩ ዜጎችም ወደ ቀያቸው እየተመለሱ መሆኑን ሌተናል ጀኔራል አስራት ገልጸዋል።
ግብረ ሃይሉ አካባቢውን ከተረከበ በኋላ በተለይ ስጋት ተፈጥሮባቸው የነበሩ አካባቢዎችን በማረጋጋት ወደ ተሻለ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለሱ መደረጉን ተናግረዋል።
በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪና የኮማንድ ፖስቱ የፖለቲካና ህዝባዊ ውይይቶች መሪ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በዜጎች ላይ ጥቃት የፈፀመውን ታጣቂ ቡድን የማደን ስራ መቀጠሉን ገልጸዋል።
የተፈፀመውን ጥቃት በመምራትና በማስተባበር የተጠረጠሩና ጥቃቱን መከላከል ሲገባቸው ሃላፊነታቸውን ያልተወጡ አመራሮች ላይ ህጋዊና ፖለቲካዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ተናግረዋል።
የጥፋት ቡድኑን አላማ ያልተቀበሉ የጉሙዝ ማህበረሰቦችን ጨምሮ በተለያዩ የማህበረሰብ አካላት ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወትማጥፋት፣ አካል ማጉደልና ንብረት ማውደም መፈፀሙን አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል።
ችግሩ እኩይ አላማ ያላቸው ሃይሎችን ብቻ የሚመለከት መሆኑን ጠቅሰው፤ “በዘላቂነት መፍትሄ ለማበጀት ግብረ ሃይሉ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው” ብለዋል።
ለተፈናቀሉ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ የማድረስና ወደ ቀዬአቸው መልሶ የማቋቋም ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም አቶ ተስፋዬ ገልፀዋል።
በሂደቱ የሰላምና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ህዝባዊ ውይይቶች እንደሚካሄዱም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.