የሀገር ውስጥ ዜና

የኦሮሚያ ክልል የግብርና ምርቶች አውደ ርዕይ እና ባዛር በአዳማ ተከፈተ

By Tibebu Kebede

January 02, 2021

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 24 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል የግብርና ምርቶችን የሚያስተዋውቅ አውደ ርዕይ እና ባዛር በአዳማ ከተማ ተከፈተ፡፡

አውደ ርዕይ እና ባዛሩ የክልሉ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በተገኙበት በአዳማ ከተማ አባገዳ አዳራሽ ተከፍቷል፡፡

በወቅቱም የክልሉ አመራሮች፣ አርሶ እና አርብቶ አደሮች እንዲሁም የግብርናው ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

በአውደ ርዕይ እና ባዛሩ ላይም የተለያዩ የግብርና ምርቶች ቀርበዋል፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ የፕሮግራሙ ዓላማ ለልምድ ልውውጥ፣ ለዘርፉ ዕድገት ድጋፍ ላበረከቱ ምሁራን እና ባለሀብቶች ዕውቅና መስጠት ነው ብለዋል፡፡

ክልሉ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ከውጪ የሚገባን ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት እና የግብርና ምርትን ወደ ውጪ በመላክ የውጪ ምንዛሪ ለማስገኘት እየሰራ መሆኑን ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

ፕሮግራሙ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚቀጥል ይሆናል፡፡

በፕሮግራሙም የፓናል ውይይት የሚካሄድ ሲሆን ለግንባር ቀደም አርሶ እና አርብቶ አደሮች፣ ለዘርፉ እድገት በምርምር አስተዋጥዖ ላበረከቱ ምሁራን እና በክልሉ በግብርና ስራ ተሰማርተው ምሳሌ ለሆኑ ባለሀብቶች ዕውቅና እና ሽልማት ይሰጣል፡፡

በሙሉ ዋቅሹሜ