Fana: At a Speed of Life!

በወ/ሮ ፍሬአለም ሺባባው የተመራ የልዑካን ቡድን በአፋር ክልል ከተለያዩ የማህበረሰብ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው

አዲስ አበባ ፣ታህሳስ 25 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሰላም ሚኒስቴር የህግ ማስከበር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬአለም ሺባባው የተመራ የልዑካን ቡድን በአፋር ክልል ከተለያዩ የማህበረሰብ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።
የልዑካን ቡድኑ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት፣ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እንዲሁም ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የተውጣጡ የአመራርና የባማለሙያዎች ቡድን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል።
የልዑካን ቡድኑ በእስከአሁን ቆይታው ገዳማይቱ፣ እንድፎ እና አዳይቱ የሚገኙ የማህበረሰብ አካላት ጋር ሰፊ ውይይት ያካሄደ ሲሆን ጉብኝቱ በሌሎች አካባቢዎችም የሚቀጥል መሆኑ ተመላክቷል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የማህበረሰቡን ፍላጎቶች እና ችግሮች በተለይም በግጭቶች ዙሪያ መሬት ላይ ያሉ ችግሮችን በግልጽ በማንሳት ሀሳባቸውን በመግለጽ በአካባቢው የሚከሰት የሰላምና የጸጥታ ችግር ምላሽና መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባም አስምረውበታል።
በውይይቱ ወቅት ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬአለም ሺባባው እንደተናገሩት ኢትዮጵያን ያስቸገራት የአመላካከት ችግር ነው÷ ኢትዮጵያ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን መብታቸው የሚከበርባትና ልጆቻችን ህልማቸውን እውን የሚያደርጉባት ሀገር ትሆናለች ብለዋል።
ለዚህም ግጭቶች ሲፈጠሩ በጉልበት ሳይሆን በማስተዋል መንቀሳቀስና በስልጡን ምክክር ማመን ያስፈልጋል ሲሉ ገልጸዋል።
አያይዘውም የህግ ማስከበር ሂደቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጻዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች ማህበረሰቡን ወክለው ላነሷቸው ጥያቄዎች ሚኒስትር ዲኤታዋ በየደረጃው ምላሽ ከሰጡ በኃላ እያንዳንዱን ጥያቄና ማሳሰቢያ መፍትሄ እንዲሰጠው የሰላም ሚኒስቴር ለሚመለከታቸው አካላት በቅደም ተከተል ያቀርባልም ብለዋል።
አያይዘውም ግጭት በሚፈጠር ጊዜ ማህበረሰቡ ለህጻናት፣ አቅመ ደካሞች እና ሴቶች ቅድሚያ ሰጥቶ ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያደርግ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በመጨረሻም በቀጠናው ጸጥታ በማስከበር ሂደት ሌተቀን እየደከሙ ላሉ የመከላከያ ሰራዊትና የፌደራል ፖሊስ አባላት ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በውይይቱ የተሳተፉ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባቶችና እናቶች፣ ሴቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች ልዑካን ቡድኑ በስፍራው በመገኘት ችግራቸውን ለማዳመጥና ለመጋራት ላሳየው ቁርጠኝነት ልባዊ ምስጋና ማቅረባቸውን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.