Fana: At a Speed of Life!

ወንጀለኞችን ለመያዝ ለሚደረገው ጥረት ሁሉ ከፀጥታ ሃይሉ ጎን መሆናቸውን የዳንጉር ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 25፣ 2013(ኤፍ.ቢ.ሲ) በመተከል ዞን በወገኖቻችን ላይ ጭካኔ በተሞላበት መልኩ ግድያ የፈፀሙ ወንጀለኞችን ለመያዝ ለሚደረገው ጥረት ሁሉ ከፀጥታ ሃይሉ ጎን መሆናቸውን የዳንጉር ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ።
በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ኃይል በመተከል ዞን የዳንጉር ወረዳ አመራሮችና የተፈናቀሉ የጉሙዝ ማህበረሰብ ተወላጆች ጋር ተወያይቷል።
ግብረ ሃይሉ በታጣቂዎች ጥቃት ቤተሰቦቻቸውን ያጡ፣ ቤታቸውና ንብረታቸው ወድሞባቸው የተፈናቀሉ የጉሙዝ ማህበረሰብ አባላትን አወያይቷል።
በውይይቱም ተደራጅቶ ጥቃት ያደረሰው ሽፍታ ቡድን በርካታ የጉሙዝ ማህበረሰብ አባላትን ጨምሮ ሌሎችንም ጭካኔ በተሞላበት መልኩ ማጥቃቱን ገልጸዋል።
“በጥቃቱ በርካታ ቤተሰቦቻችንን አጥተናል፣ ንብረታችንን አጥተናል፣ ቤታችን ተቃጥሎብን አሁን በጣም ከባድ ችግር ላይ ነው የምንገኘው” ብለዋል።
በመሆኑም የጋራ ጠላታችን የሆነውን የታጠቀ ሃይል ለመያዝ ለሚደረገው ጥረት ሁሉ ከፀጥታ ሃይሉ ጎን ነን ሲሉ አረጋግጠዋል።
በግብረ ሃይሉ የሕግ ማስከበርና የፀጥታውን ዘርፍ የሚመሩት ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ፤ የታጠቀውን ሃይል በማደን ለህግ ለማቅረብ የተጠናከረ ዘመቻ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ ሂደት የአካባቢው ነዋሪ እያደረገ ያለውን ትብብር አድንቀው ወንጀለኞችን ለመያዝ በሚደረገው ጥረት ትብብሩን እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል።
አሁን ላይ ወንጀለኞች መያዝ መጀመራቸውን የገለጹት ሌተናል ጄኔራል አስራት በስጋት የሸሹ የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ችግሩን ለመፍታት ከሃገር ሽማግሌዎች፣ ከነዋሪዎችና ከሃይማኖት አባቶች ጋር የሚካሔደው የቅንጅት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ሌተናል ጄኔራል አስራት ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.