Fana: At a Speed of Life!

መሪ እቅዱ ቀጣይነት ያለው የፋይናንስ ተቋማት እድገት አካታችና ጥራት ያለው የምጣኔ ሃብት ለውጥ ምሰሶዎችን የያዘ ነው -ዶክተር ፍጹም አሰፋ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 26፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአስር አመቱ የልማት መሪ እቅድ አካታችና ጥራት ያለው ምጣኔ ሃብት እድገት፣ ቀጣይነት ያለው የፋይናንስ ተቋማት እድገት፣ የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታና የዲጂታል ኢኮኖሚ እድገት ምሰሶዎችን ያካተተ ነው  ሲሉ የብሔራዊ ፕላንና ልማት እቅድ ኮሚሽነር ዶክተር ፍጹም አሰፋ ገለጹ።

የብሔራዊ  ልማትና እቅድ ኮሚሽነሯ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በፖሊሲ ማተር ቆይታ አድርገዋል።

በቆይታቸው  ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች እድገት ብታስመዘግብም የተመዘገቡት ለውጦች ግን እያንዳንዱ ዜጋን ተደራሽ ያደረጉ ባለመሆናቸው  በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ የዴሞክራሲና የተጠቃሚነት ጥያቄዎች ማስነሳቱን ገልጸዋል።

በዚህም እያደገ ያለው ኢኮኖሚ  ሁሉን አካታች እንዲሆንና የተጠቃሚነት ጥያቄዎችን ለመመለስ የለውጥ ስራ መስራት አስፈልጓል ነው ያሉት።

አሁን እየተከናወነ ያለው የአስር አመት መሪ እቅድም ድህነትን በግመሽ በመቀነስ ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካለቸው አገራት ተርታ ለማሰለፍ ያለመ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ፖሊሲው የስራ አጥ ቁጥርን 9 በመቶ ለማድረስ እንደሚሰራና በመሰረተ ልማት  ዘርፍም ሰፊ ተግባራት እንደሚከናወኑ አስታውቀው÷ ለአብነትም በሃይል ልማት ዘርፍ በከተማና በገጠር 20 ጊጋ ዋት ሃይል ለማመንጨት መታቀዱን ጠቁመዋል።

በማህበራዊ ዘርፉ ደግሞ በጤና፣ በትምህርትና በአቅም ግንባታ ተግባራት ላይ ፖሊሲው እንደሚያተኩርና ሌሎችንም ግቦች ያካተተ ነው ብለዋል።

ይህንን ለማሳካት መሪ እቅዱ ሰፊ ምሰሶዎችን መያዙን ጠቁመው አካታች እና ቁልፍ ጥራት ያለው የምጣኔ ሃብት እድገት፣ የተናጠል ግብና ምርታማነት፣ ቀጣይነት ያለው የፋይናንስ ተቋማት እድገት፣ የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታና ዲጂታል ኢኮኖሚ እድገት መካተቱን አስረድተዋል።

የግል ሴክቴሩን ከፊት ቀዳሚ ማድረግ፣ አረንጓዴ ልማት፣ ተቋማዊ ግንባታ እንዲሁም የፍትህና ህዝባዊ አገልግሎት ማግኘት፣ ማህበራዊ አካታችነትና ማብቃት፣ በቀጠናው አካባቢ ልማትና ትስስር መፍጠር እንዲሁም  የጸጥታና ደህንነት ግንባታ ምሶሶዎችን መሪ እቅዱ ማካተቱን ነው የገለጹት።

የመንግሰት እቅድ ብቻ ሳይሆን ህዝቡንና ባለ ድርሻ አካላትን እንዳካተተ የገለጹት ዶክተር ፍጹም ÷ ቀድሞ ተሰርቶ የሚሰጥ ሳይሆን ተቋማትና በላድርሻ አከላት ራሳቸው የሚያዘጋጁት ነው ብለዋል።

መሪ እቅዱ ከ100 በላይ ከፍተኛ አማካሪዎች ጋር በመሆን መዘጋጀቱን ገልጸው÷ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ውጤትን መሰረት ያደረገ ምዘናን በስሩ ያካተተ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.