Fana: At a Speed of Life!

ከፍተኛ ገንዘብ በመቀበል በህገወጥ መንገድ ወደ ውጪ ሀገር ሲልኩ የነበሩ የኢምግሬሽን አመራሮችና ሰራተኞች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 26፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ህጋዊ መንገድ ማሟላት ካልቻሉ ዜጎች ገንዘብ በመቀበል በህገወጥ መንገድ ወደ ውጪ ሀገር ሲልኩ የነበሩ የኢምግሬሽን አመራሮችና ሰራተኞች እንዲሁም በህጋዊ አሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ስም የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ የኢምግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነቶች ኤጀንሲ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቅርንጫፍ የሚሰሩ አመራሮችና ሰራተኞች በህጋዊ መንገድ ሰዎችን ወደ ውጪ ሀገር ለመላክ ከተቋቋሙ አሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ጋር የጥቅም ትስስር በመፍጠርና በመመሳጠር ህጋዊ ሂደቶችን ያላሟሉና ከሀገር መውጣት የማይገባቸውን ግለሰቦች በህገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ሲያስወጡ ነበር፡፡
የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ቡድን ጋር ባደረጉት የተቀናጀ ክትትልም በህገወጥ ድርጊቱ ሲሳተፉ እንደነበር የተጠረጠሩ 21 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ አድርገዋል፡፡
የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ መግለጫ እንዳብራራው በአሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ስም ተደራጅተው በዚህ ተግባር የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ህጋዊ መንገዱን አሟልተው ከሀገር መውጣት ካልቻሉ ዜጎች ከፍተኛ ገንዘብ በመቀበል ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ኢምግሬሽን ቅርንጫፍ ከሚሰሩና በጥቅም ከተሳሰሯቸው አመራሮችና ሰራተኞች ጋር በመከፋፈል ሰዎች በህገወጥ መንገድ ከሀገር እንዲወጡ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡
በሶስት ተጠርጣሪ የኢምግሬሽን ባለሙያዎች ቤት በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻም ከ1ሚሊየን ብር በላይ እንዲሁም የተለያዩ የባንክ ደብተሮችና ሰነዶች መገኘታቸውን ያመለከተው መግለጫው በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ከተጠረጠሩ ሶስት በአሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ስም ከሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ቤትም የሌሎች ሰዎች ሰባት ፓስፖርቶች ተይዘዋል፡፡
በአጠቃላይ በተጠርጣሪዎች ቤት በተደረገ ፍተሻ 37 የባንክ ደብተሮችና ለህገ ወጥ ስራቸው የሚጠቀሙባቸው የተለያየ ቁሳቁስ የተገኙ ሲሆን ተጨማሪ የማጣራት ስራዎችም እየተከናወኑ ነው፡፡
በህገ-ወጥ ተግባሩ በአሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ስም የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች የኢምግሬሽን ባለሙያዎችና አመራሮች ምስጢራዊ የጥቅም ትስስር ዘርግተው እንደነበር የሚጠቁሙ መረጃዎች መገኘታቸውን መግለጫው አመልክቷል።
የጥቅም ትስስሩ ከፍተኛ ኔትወርክ ያለው በመሆኑም በህግ የሚፈልጉ እና ከሀገር እንዳይወጡ የተከለከሉ ግለሰቦች ጭምር በቀላሉ እንዲወጡ ሰፊ እድል እንደሚፈጥር በህጋዊ መንገድ በማይወጡ ዜጎች ላይ እንግልት እንደሚያስከትልና የመንግስትን ገቢ እንደሚያሳጣም ተገልጿል።
የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ጋር በመቀናጀት በቁጥጥር ስር ካዋሏቸው ተጠርጣሪ ግለሰቦች መካከል አስራ ስድስቱ የኢምግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነቶች ኤጀንሲ አመራርና አባላት ሲሆኑ÷ አምስቱ ሰዎችን ወደ ውጭ ሀገራት የሚልኩ የአሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ሰራተኞች መሆናቸው ታውቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ተጠርጣሪዎቹ እንዲህ አይነቱን ህገወጥ ሰንሰለት ተጠቅመው የስግብግቡ ጁንታው ቡድን አባላትን ጭምር ሳይቀር ከሀገር ለማስወጣት እንዳይጠቀሙበት አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ አስቀድሞ ኔትወርካቸውን የመበጣጠስ ስራዎች መስራቱን አስታውቋል፡፡
በተያያዘም የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አመራሮችና ባለሙያዎች ከሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ጋር ተቀናጅተው በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በተለይ በትግራይ፣በቤንሻጉል ጉምዝና በአፋር ክልሎች በህግ ማስከበር ዘመቻው ሂደት ስምሪት ወስደው በመንቀሳቀስ የሃገርን ብሔራዊ ደህንነትና ጸጥታ ለማረጋገጥ እየሰሩ መሆኑን ያስታወቀው መግለጫው በዚህ ሂደትም ተጨባጭ ውጤቶችም መገኘታቸውን አመልክቷል፡፡
በቀጣይም ህዝብና መንግስት የጣለባቸውን አደራና ሀላፊነት ወደ ጎን በመተው በወንጀል ድርጊት የሚሳተፉ በየትኛውም የኃላፊነት ደረጃና መዋቅር ላይ ያሉ ተጠርጣሪዎችን ተከታትሎ በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መረጃ ገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም ህብረተሰቡ በእንደዚህ አይነት የወንጀል ድርጊቶች ላይ የሚሳተፉ ግለሰቦችን ሲመለከት በአቅራቢያው ለሚገኙ የደህንነትና የፀጥታ ተቋማት አስፈላጊውን ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.