Fana: At a Speed of Life!

ምክትል /ጠ/ሚ ደመቀ መኮንን በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለዲፕሎማቶች ማብራሪያ ሰጡ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 26፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለአምባሳደሮች፥ ሰብአዊ እና የመልሶ ማቋቋም ለጋሾች ቡድን ተወካዮች በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ውይይቱ የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሬድዋን ሁሴን፣ብሔራዊ የአደጋ መከላከል አስተዳደር ኮሚሽነር ምትኩ ካሣ እና የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳዮች አስተዳደር ዳይሬክተር በተገኙበት ነው የተካሄደው።

በመድረኩም ለሰብአዊ እና የመልሶ ማቋቋም ለጋሾች ቡድን አባል ሀገራት ምስጋና ቀርቧል።

በትግራይ ክልል የምግብ ፍጆታዎችና የህክምና ቁሳቁሶች አቅርቦት እየቀረበ መሆኑን የገለጹ ሲሆን ፤ የሰብአዊ ዕርዳታ አሰጣጡም በታቀደው መሠረት እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በኢትዮጵያ መንግስት እና በተባበሩት መንግስታት ስምምነት መሰረት እና አሁን ያለውን የማስተባበር ዘዴ በመጠቀም የሰብአዊ ዕርዳታ አቅርቦት እንደታሰበው እየሄደ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል ፡፡

በህወሓት ጁንታ የመሠረተ ልማት አውታሮች ላይ የደረሰውን ከባድ ውድመት ያስታወሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአሁኑ ወቅት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በሙሉ የቴሌኮሙዩኒኬሽን መስመሮችን መልሶ የመገንባት ስራ እየተሰራ መሆኑን ለአምባሳደሮች ገለፃ አድርገዋል፡፡

በተጨማሪም የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ከለጋሽ ማህበረሰቦች ጋር ተቀራርበው በመስራት ላይ መሆናቸውን ገልፀው የስደተኞችን እና የሰብዓዊ እርዳታ የሚፈልጉትን ጉዳዮች በብቃትና በወቅቱ ለመፍታትም ይህንኑ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

ጊዜያዊ አስተዳደሩም በክልሉ ያሉ ህዝብ የልማት ፍላጎቶች በብቃት እንዲመልስ ህብረተሰቡን በማሳተፍ የክልሉ የተለያዩ የአስተዳደር እርከኖች አስፈላጊ አገልግሎቶችን እንዲሰጡ ለማድረግ ያለመታከት እየሰራ ነው ብለዋል ፡፡

በስብሰባው ላይ የተገኙት ሚኒስትሮች እና ሌሎች የመንግስት ባለስልጣናትም በትግራይ የተፈጠረውን ሰብዓዊ ሁኔታ ለመቅረፍ እየተሰራ ስላለው ስራ ዝርዝር መረጃ አቅርበዋል፡፡

በክልሉ የሚከናወኑ የሰብአዊ እንቅስቃሴዎችን የበለጠ ለማሳደግ በጋራ ለመስራት ከቡድኑ ጋር ያለውን ግንኙነት ለመቀጠል ግንዛቤ ተፈጥሯል ፡፡

አምባሳደሮቹ የኢትዮጵያ መንግስት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር መረጃ ለመስጠት ቅድሚያውን በመወሰዱ አድናቆታቸውን መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.