Fana: At a Speed of Life!

የመገናኛ ውሀ ልማት – ቦሌ ወረዳ 17 ጤና ጣቢያ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ በተያዘው በጀት ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 27 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የመገናኛ ውሀ ልማት – ቦሌ ወረዳ 17 ጤና ጣቢያ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ በተያዘው በጀት ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን አዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

ይህ የመንገድ ፕሮጀክት ቀደም ሲል 800 ሜትር የሚሆነው የመንገዱ ክፍል ላይ የቴሌ ኦፕቲክ ፋይቨር ኬብሎች፣የኤሌክትሪክ መብራት ምሰሶዎች እና ቤቶች በወቅቱ ባለመነሳታቸው የግንባታ ስራው በተፈለገው መጠን እንዳይከናወን እንቅፋት ሆነው መቆየታቸው ባለስልጣኑ የገለፀው፡፡

አሁን ላይ ባለስልጣኑ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ችግሩ እንዲፈታ በማድረጉ አሁን ላይ የመጀመሪያ ደረጃ አስፋልት ንጣፍ እና የእግረኛ መንገድ ስራ ተጠናቋል ተብሏል፡፡

ባለስልጣኑ የመንገድ ፕሮጀክቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ የሁለተኛ ደረጃ የአስፋልት ንጣፍ እና የእግረኛ መንገድ የማስተካከያ ስራዎችን ሙሉ በሙሉ አጠናቆ ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቱ አጠቃላይ 1 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና 20 ሜትር የጎን ስፋት ያለው ሲሆን ሀፍኮን ኮንስትራክሽን ከ 84 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ግንባታውን እያከናወነው ይገኛል፡፡

የማማከርና የግንባታ ቁጥጥሩን ስራውን ደግሞ ቤስት አማካሪ ድርጀት ነው እየሰራው የሚገኘው፡፡

የመንገዱ ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላ ከመገናኛ ወደ 24 ቀበሌ እና አንበሳ ጋራዥ አካባቢ ለሚደረገው እንቅስቃሴ አማራጭ መንገድ ሆኖ ከማገልገሉም በተጨማሪ መገናኛ አካባቢ እየጨመረ የመጣውን የትራፊክ መጨናነቅ ለማቃለል ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.