Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ለኢትዮ ሱዳን የድንበር ልዩነት ጦርነት መፍትሄ አይደለም ብላ ታምናለች – አምባሳደር ዲና

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 27 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ጦርነት ለኢትዮ ሱዳን የድንበር ልዩነቱ መፍትሄ አይደለም ብላ እንደምታምን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለፁ።

ቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ሳምንታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ  ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው ከኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር ጋር በተያያዘ ያለውን ጉዳይ የሚከታተል የድንበር ኮሚሽን እና ባለሙያዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ ኢትዮጵያ ሃገራቱ ወደነበሩበት ውይይት እንመለስ የሚል አቋም እንዳላት ያነሱት ቃል አቀባዩ፥ ጦርነት ለድንበር ልዩነቱ መፍትሄ አይደለም ብላ ታምናለችም ነው ያሉት፡፡

ሆኖም የድንበር ሉዓላዊነቷን ለማሥከበር ጠንካራ ስራዎችን ታከናውናለች ብለዋል ቃል አቀባዩ።

አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው ለአንድ ወር ተቋርጦ የነበረው የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ውይይት ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።

በወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊመቀንበር በደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ የተሰየሙ ባለሙያዎች ባቀረቧቸው ሰነዶች ላይ ውይይት እየተካሄደ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ባለፈው እሁድ በነበረው የሶስትዮሽ ውይይት መቋጫ ላይ በቀረበው ሰነድ ላይ ኢትዮጵያና ሱዳን ሲስማሙ ግብፅ አልተስማማችም ብለዋል።

እሁድ በነበረው ውይይት ላይ ሀገራቱ እስከአሁን የነበሯቸውን ልዩነቶች እና ስምምነቶች ባለሙያዎች እንዲያቀርቡ በሚል ውይይቱ ቢቋጭም በትናንትናው ዕለት ሱዳን ባለመገኘቷ ውይይቱ አለመካሄዱንና  ጉዳዩን በተመለከተም ለሰብሰቢዎቹ ሪፖርት መደረጉን አስረድተዋል።

ዛሬን ጨምሮ በቀጣይ ቀናት  ሱዳን በውይይቱ ላይ ለምን እንዳልተገኘች መልስ ትሰጣለች ተብሎ እየተጠበቀ መሆኑንም አምባሳደሩ አስታውቀዋል።

ነገር ግን በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚካሄደው የሶስትዮሽ ውይይት አሁንም ይቀጥላል ነው ያሉት አምባሳደር ዲና።

በፍሬህይወት ሰፊው

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳ
የፋና ድረ ቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.