Fana: At a Speed of Life!

በዩኒቨርሲቲዎች በተከሰቱ ግጭቶች የተሳተፉ ከ170 በላይ ተማሪዎች የ1 ዓመት እገዳና እስከ መጨረሻ ከትምህርታቸው እንዲሰናበቱ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 26፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተከስቶ በነበረው ግጭት እጃቸው አለበት ተብለው በተለዩ ከ450 በላይ በሚሆኑ ተማሪዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱ ተገለፀ፡፡

በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተከስቶ የነበረውን ግጭት እና ሁከት አስመልክቶ የሳይንስ እና ከፍተኛ የትምህር ሚኒስቴር ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመሆን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

መግለጫውን የሰጡት የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ እና የፌዴራል ፓሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር መላኩ ፈንታ ናቸው፡፡

በመግለጫውም ባለፉት 15 ቀናት ብቻ ከ170 በላይ ተማሪዎች ከአንድ አመት እስከ መጨረሻ የሚደርስ የማባረር አስተዳደራዊ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ተጠቁሟል፡፡
እንዲሁም ከ280 በላይ የሚሆኑት ተማሪዎች ላይ ደግሞ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

በሁከቱ የደረሰውን ችግር መፍትሄ እንዲያገኝ ለማድረግም ፌዴራል መንግስት እና ክልሎች እንዲሁም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ከተውጣጡ አካላት ጋር በመሆን ግምገማ ሲደረግ መቆየቱ ነው የተነገረው፡፡

በተደረገው ግምገማም ለሁከቱ እና ለችግሩ ምክንያት ናቸው ተብለው በተለዩ አካላት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲውሰድ ተደርጓል ተብሏል፡፡

በዚህም በወንጀል የተሳተፉትን በህግ ተጠያቂ ማድረግ እንደተጠበቀ ሆኖ የትምህርት ተቋማቱ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዳቸው በመግለጫው ላይ ተነስቷል፡፡

በችግሩ ተሳትፈዋል ተብለው ከተለዩ ተማሪዎች ባለፈም መምህራን እና የትምህርት ተቋማቱ የአስተዳደር ሰራተኞች ተሳታፊ እንደነበሩ መለየት መቻሉ ተጠቁሟል ፡፡
ይህንን ተከትሎ ከአስር በላይ መምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞች የስራ ውላቸው ተሰርዟል ነው የተባለው፡፡

አሁን ላይ የተወሰኑት የትምህር ተቋማት ሙሉ በሙሉ ወደ መደበኛ የመማር ማስተማሩ ሂደታቸው መመለስ መቻላቸውም ተነስቷል፡፡

ቀሪውን የትምህርት ጊዜ ወደነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስም ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በመሆን የክትትል ስራ ይሰራል ተብሏል፡፡

አሁን ላይ የሚታዩ ግጭቶች በትምህርት ተቋማቱ ብቻ ተወስነው ሊቀሩ እንደማይችሉ በመገንዘብ ለሚደረገው ሰላምን የማረጋገጥ ስራ ህብረተሰቡም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል፡፡

በይስማው አደራው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.