Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ የከባቢ አየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እየተከናወኑ የሚገኙ የተፋሰስ ልማት ስራዎችን ህብረተሰቡ አጠናክሮ መቀጠል አለበት- አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

አዲስ አበባ ፣ታህሳስ 27 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በጋምቤላ ክልል የከባቢ አየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እየተከናወኑ የሚገኙ የተፋሰስ ልማት ስራዎችን ህብረተሰቡ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለፁ፡፡
“የተፋሰስ ልማት ለግብርና እድገት” በሚል መሪ ቃል የተፋሰስ ልማት የንቅናቄ መድረክ የክልል፣ የዞንና፣ የወረዳ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል፡፡
በወቅቱም ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ÷በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ የአየር ንብረት ተጽዕኖ ሊያመጣ የሚችለውን ጉዳት ለመከላከል በርካታ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል ብለዋል፡፡
በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሀሳብ አመንጭነት በሀገሪቱ አራት ዓመታት 20 ቢሊየን ችግኞችን የመትከል ግብ ተቀምጦ ስኬታማ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡
ክልሉም በ2011 እና በ2012 የበጀት ዓመት 10 ነጥብ 6 ሚሊየን ችግኝ ተከላ በማከናወን ድርሻውን በስኬት መወጣቱን ጠቅሰው÷ በ2013 በጀት ዓመት 6ነጥብ 5 ሚሊየን ችግኝ የማዘጋጀት ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በመሆኑም የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሶ በማልማትና በመጠበቅ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት በየደረጃው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፏቸውን ሊያሳድጉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡጁሉ ሉዋል በበኩላቸው÷ በክልሉ ባለፉት ዓመታት ህብረተሰቡን በማሳተፍ በተከናወኑ ተግባራት የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ጠቁመው የተገኙ ምርጥ ተሞክሮዎችን ከማስፋት አንፃር ውስንነቶች መኖራቸውን አብራርተዋል፡፡
የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራው የአካባቢ መራቆትን ከመከላከል፣ የአፈር ለምነትን ከመጠበቅና ምርታማነትን ከማሳደግ በተጨማሪ የብዝሃ ህይወትን ህልውና ጠብቆ ለማቆየት ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ሞላም በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተሰሩ የተፋሰስ ልማት ስራዎች በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ተራቁተው የነበሩ ቦታዎች መልሰው ማገገማቸውን ጠቁመዋል፡፡
በዘንድሮው በጀት ዓመት በክልሉ በሁሉም ወረዳዎች 32 አዲስ የማህበረሰብ ተፋሰሶችን በማልማት ከ18 ሺህ ሄክታር በላይ መሬቶችን ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነፃ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በክልሉ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት እንደሚገኝ የጠቆሙት አቶ ካሳሁን በበጋው ወራት የተፋሰስ ልማት ስራውን ለማከናወን የህብረተሰቡ ግንዛቤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
በተፋሰስ ልማት የንቅናቄ መድረኩ የክልል፣ የዞንና፣ የወረዳ ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸውን ከክልሉ ፕሬስ ሰክሬተሪያት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.