Fana: At a Speed of Life!

የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች ተጎጂዎችን ሊጎበኙ ነው

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 27፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች የጸጥታ ችግር ተከስቶባቸው ወደነበሩ የሃገሪቷ አካባቢዎች በማቅናት ከተጎጂዎችና ከአካባቢ ማኅበረሰብ ጋር ሊወያዩ መሆኑ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤና የኢትዮጵያ የሃገር ሽማግሌዎች መማክርት ዛሬ በጉዳዩ ላይ የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የጉባኤው ዋና ጸሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ በአገሪቷ ባለፉት ጊዜያት በተከሰቱ የጸጥታ ችግሮች የዜጎች ሕይወት መጥፋቱን፣ በርካቶች ከቀዬአቸው መፈናቀላቸውንና ንብረታቸውም መውደሙን አንስተዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤና የሃገር ሽማግሌዎች መማክርት እነዚህን ተጎጂዎች ለመጎብኘትና ለመወያየት ውሳኔ ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

በነገው ዕለትም ወደ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን በማቅናት ውይይቱ በይፋ እንደሚጀመር ጠቁመዋል።

ቁጥራቸው 25 የሚሆኑ የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎችን ያካተተው የልዑካን ቡድን ወደ ሥፍራው አቅንቶ ተጎጂዎችን እንደሚያነጋግርም አስታውቀዋል።

ጉብኝቱ በዋናነት ተጎጂዎችን ማግኘት፣ ማወያየትና ማጽናናት ዓላማ ያደረገ ሲሆን ተጎጂዎቹ የደረሰባቸውን ጉዳት በመለየት ድጋፍ ለማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ምክክር እንደሚደረግ ነው ዋና ጸሐፊው የገለጹት።

ጎን ለጎንም አገር በቀል እውቀቶችና ክህሎቶች የጸጥታ ችግሮችን አስቀድሞ ለመከላከል እንዲሁም ግጭት ከተከሰተ በኋላ እንዳይዛመት ለማድረግ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ይሰራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌዎች መማክርት ምክትል ሰብሳቢ ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ በበኩሉ “የተከሰቱ የጸጥታ ችግሮች መደገም የለባቸውም” ብሏል።

ለዚህም ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንዳለበት ጠቁሞ፤ የጥላቻ መልዕክት የሚያስተላልፉ ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸው አስገንዝቧል።

በተለይም በመገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ መልዕክቶች ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግባቸው እንደሚገባና በኃላፊነት ስሜት መሆን እንዳለበት አመልክቷል።

“የጉብኝት መርሃ ግብሩ ስኬታማ እንዲሆን ማኅበረሰቡ፣ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎችን ሊሰማ ይገባል” ብሏል።

ህብረተሰቡ የቆየ የአብሮነትና የአንድነት እሴቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ በጋራ ጥምረቱ በኩል በትኩረት እንደሚሰራም በመግለጫው መጠቀሱን ኢዜአ ዘግቧል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.