Fana: At a Speed of Life!

የመተከል ግጭት የህዳሴ ግድብን ለማስተጓጎል የታለመ መሆኑን በመገንዘብ ለመፍትሄው ሊሰራ እንደሚገባ ተገለፀ

አዲስ አበባ ፣ታህሳስ 30 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና ሃገር ሽማግሌዎች መማክርት ጥምረት ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሃገር ሽማግሌዎች ጋር በአሶሳ  ከተማ ተወያይተዋል፡፡

የሃገር ሽማግሌዎች ተወካይ ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ  እንዳሉት ÷ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኢትዮጵያውን አሻራ ያረፈበት የህዳሴው ግድብ መገኛ ነው፡፡

ክልሉ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ማብሰሪያ ነው፤ በአካባቢው ተደጋጋሚ ግጭት እንዲነሳ የሚደረግበትም ምክንያት ይኸው ነው ያሉ ሲሆን ፕሮጀክቱ ቢደናቀፍ የመጀመሪያ ተጎጂ የቅርብ ተጠቃሚ የሆነው የክልሉ ህዝብ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የሃገር ሽማግሌዎች በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ሲዘዋወሩ በየቦታው የሚከሰቱ ግጭቱ ዘላቂ መፍትሔ እንዲኖረው አመራሮች በሃላፊነት እንዲሠሩ ጥያቄ እንደሚያቀርብ ጠቁመዋል፡፡

ሁሉም አመራር የሚመራውን ህዝብ ደህንነት መጠበቅና መገናኛ ብዙሃንም ግጭትን ከማራገብ ሊቆጠቡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና የሃገር ሽማግሌዎች ጥምረት ምክትል ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በበኩላቸው  የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በህዳሴው ግድብ ምክንያት የዓለምን ትኩረት ስቧል ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በክልሉ ትምህርት እና መሠረተ ልማት በሚገባ ያላገኙ ነዋሪዎችንም ህይወት ይቀይራል ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን ኀብረተሰቡ በክልሉ ተደጋጋሚ ግጭት እንዲነሳ የሚደረገው የልማቱ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ለማድረግ እንደሆነ መረዳት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ሃገር ሽማግሌዎች እንደ ክልል ብቻ ሳይሆን እንደሃገር የገጠመውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት የሃይማኖት አባቶች፣ ቤተሰብ፣ ትምህርት ቤት እና መንግስት የሚጠበቅባቸውን መወጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡

የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር አዳሙ ጅባት እንዳሉት ክልሉ በሚጠበቅበት ደረጃ አለመልማት ለጸረ ሠላም ሃይሎች ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልፀው ህገወጥ የጦር መሳሪያንም መቆጣጠር እንደሚያስፈልግ እንዲሁም ለወጣቱ ስራ እድል መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ ተቀዳሚ ሙፍቱ ሃጂ ኡመር የሰው ልጅ በሰውነቱ ሊከበር እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት ስለመተከል ግጭት ግንዛቤ ማግኘታቸውን የተናገሩት ሙፍቱ ሃጂ ኡመር ፤ መንግስት እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ለችግሩ የመፍትሔ እርምጃ እንዲወስዱ እንሠራለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ሃገራችን በብዙ ፈተና ውስጥ ናት ያሉት በኢትዮጵያ የሃይማኖት ጉባኤ እና የሃገር ሽማግሌዎች መማክርት ጥምረት ሰበሃገሪቱ ሞት እና ስደት እንዲበቃ ሁላችንም በአንድ ሃሳብ መስራት አለብን ሲሉ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.