Fana: At a Speed of Life!

የቡሬ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመጀመሪያ ምእራፍ ግንባታ 96 በመቶ ደረሰ

አዲስ አበባ ፣ታህሳስ 30 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የቡሬ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ሂደት 96 በመቶ መድረሱ ተገለጸ።
የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በስጋ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የቅባት እህሎች፣ የማርና የወተት ተዋጽኦ ማቀናበሪያ ኢንዱስትሪ ላይ የሚሰማሩ ባለሃብቶችን ለመቀበል ዝግጅት ማጠናቀቁ ተገልጿል።
ዓለም አቀፍ ደረጃን ጠብቆ እየተገነባ የሚገኘው ፓርኩ አሁን ላይ ለቢሮ፣ ለመጋዘን፣ ለካፍቴሪያ እና ለአንድ መስኮት አገልግሎት የሚሆኑ የህንጻ ግንባታዎችን አጠናቋል ነው የተባለው።
በግብርናው ዘርፍ የተሻለ ቴክኖሎጂን ያመጣል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ይህ በግብርና ምርቶች ማቀነባር ዘርፍ ላይ የሚሰማሩ ባለሃብቶችን የሚጋብዘው ኢንዱስትሪ ፓርክ ለማምረቻ የሚሆኑ ሞዴል ሼዶችንም ገንብቶ አጠናቋል።
እስካሁንም የግብርና ምርቶችን በግብአትነት የሚጠቀሙ 12 አምራቾች ፕሮጀክት ጥያቄ ማቅረባቸውን የፓርኩ ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ ዳኛቸው አስረስ ገልፀዋል ።
3 አምራች ፋብሪካዎች ወደ ስራ ገብተዋል ያሉት ዋና ስራ አስኪያጁ ፓርኩ አሁን ላይ 3 ሺህ ለሚሆኑ የአካባቢው ወጣቶች የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ሲገባ ለ50 ሺህ ወጣቶች የስራ እድልን እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
በተጨማሪም በፓርኩ የሚተከሉ ፋብሪካዎች ከገበሬው የግብርና ግብአቶችን በመግዛት በአካባቢው የሚስተዋለውን የምርት ብክነት ይቀንሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የገጠርና ከተማን ትስስር በመፍጠር ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ የሚኖረው ይህ ኢንዱስትሪ ፓርክ የራሱ የሆነ የሃይል ምንጭ የሚፈልግ በመሆኑ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት አምራቾች ወደ ምርት ሂደት እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል።
በቆንጂት ዘውዴ

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.