Fana: At a Speed of Life!

የጥፋት ስትራቴጂስቱና ዋነኛው የጁንታ መሪ ስብሃት ነጋ በቁጥጥር ስር ዋለ

አዲስ አበባ ፣ታህሳስ 30 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጥፋት ስትራቴጂስቱና ዋነኛው የጁንታ መሪ ስብሃት ነጋን ጨምሮ ሌሎች የጥፋት ቡድኑ አመራሮች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የሀገር መከላከያ ሰራዊት ገለፀ።
በአገራችን ላለፉት 27 አመታት የማተራመስ ስትራቴጂ የነደፈ ያስተባበረና ያደራጀ በመጨረሻም ጦርነት እንዲቀሰቀስ በማድረግ በሀገራችን ሰራዊት ላይ እጅግ ዘግናኝ ጦርነት በመክፈት ሰራዊቱን ያስጨፈጨፈው የጁንታው ቁንጮ፣ ስብሃት ነጋ በቁጥጥር ስር ውሏል።
የመከላከያ ሰራዊት ኃይል ስምሪት መምሪያ ኃላፊ ብርጋዴል ጀነራል ተስፋዬ አያሌው ለኢዜአ እንደገለፁት፣ የጁንታው ቁንጮ አመራር ስብሃት ነጋ ከተደበቀበት ለሰው ልጅ እጅግ አስቸጋሪ የሆነ ሰርጥ ውስጥ በቁጥጥር ስር ውሏል።
የጁንታውን ቁንጮ ስብሀት፣ የጥፋት ቡድኑ አባላት በሰርጡ ውስጥ ተሸክመው በማስገባት ደብቀውት እንደነበር ብርጋዴል ጀነራል ተስፋዬ ገልፀው፣ ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የፌዴራል የፀጥታ አካላት በጋራ ባደረጉት ፍተሻና አሰሳ፣ ከተደበቀበት በማውጣት በቁጥጥር ስር አውለውታል።
በተጨማሪም ከመከላከያ የከዱ ሌሎች ከሃዲ የጁንታው ቡድን አመራሮች ከጁንታው መሪ ስብሃት ነጋ ጋር አብረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አመልክተዋል።
እነዚሁ ከመከላከያ የከዱ የጁንታው ቡድን አመራሮች የጁንታውን ታጣቂ ሀይል በማዋጋትና በማሰልጠን እኩይ ዓላማቸውን ለማስፈፀም ሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቁመው፣ በመጨረሻም የጁንታውን አመራር ዙሪያ ጥበቃ ሲያስተባብሩ ቆይተው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የመከላከያ ሰራዊት ኃይል ስምሪት መምሪያ ኃላፊ ብርጋዴል ጀነራል ተስፋዬ አያሌው ለኢዜአ ገልፀዋል።
እነዚህኑ የጁንታው አመራሮች ለመከላከል በአካባቢው ጥበቃ ላይ የነበረ የጁንታው ታጣቂ ሀይልም መደምሰሱን ተናግረዋል።
በዚሁ መሰረት በቁጥጥር ስር የዋሉት፣
1. የጁንታው ቁንጮ አመራርና የጥፋት ስትራቴጂስት፣ ስብሃት ነጋ
2. ሌተናል ኮሎኔል ፀአዱ ሪች- የስብሃት ነጋ ባለቤትና ቀደም ሲል በጦር ሃይሎች ሆስፒተል ሃኪም የነበረች፣ በኋላም በጡረታ የተገለለች
3. ኮሎኔል ክንፈ ታደሰ- ከመከላከያ የከዳ
4. ኮሎኔል የማነ ካህሳይ- ከመለካከያ የከዳ
5. አስገደ ገ/ ክርስቶስ- ከመሃል ሀገር ተጉዞ ቡድኑን የተቀላቀለና ለጊዜው ሃላፊነቱ ያልታወቀ ግለሰብ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን
6. የሜጀር ጀነራል ሃየሎም አርአያ ባለቤት የነበረችና ኑሮዋን በአሜሪካ አድርጋ የቆየች በኋላም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ወደ ጁንታው ተቀላቅላ የነበረች፣ ወይዘሮ አልጋነሽ መለስ ጁንታውን በመያዝ ኦፕሬሽን ሂደት ውስጥ ለማምለጥ ስትሞክር ገደል በመግባት ህይወቷ ማለፉን ብርጋዴል ጀነራል ተስፋዬ አያሌው ገልፀዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.