ሺንዞ አቤ በመካከለኛው ምስራቅ ሃይል የማስፈር እቅድ እንዳላቸው በድጋሚ ገለጹ
አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 27 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ በመካከለኛው ምስራቅ ሃይል የማስፈር እቅድ እንዳላቸው በድጋሚ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የጃፓን መርከቦችን ደህንነት ለማረጋገጥ በስፍራው ሃይል የማስፈር እቅድ እንዳላቸው ገልጸዋል።
ባለፈው ወር ጃፓን ወደ መካከለኛው ምስራቅ የጦር መርከቦችን እና ቃኝ አውሮፕላኖችን እንደምትልክ ገልጻ ነበር።
የሃገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴርም ቃኝ አውሮፕላኖቹ በተያዘው የፈረንጆቹ ጥር ወር ወደ ስፍራው እንደሚያቀኑ ገልጿል።
የካቲት ወር ላይ ደግሞ የጦር መርከቦችን ወደ ስፍራው አንቀሳቅሳለሁ ብሏል።
የአሁኑ የቶኪዮ እቅድ በመካከለኛው ምስራቅ የባህር ክልል የሚንቀሳቀሱ የጃፓን መርከቦችን ከጥቃት ለመከላከልና ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ ያለመ ነው ተብሏል።
አቤ በንግግራቸው በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ እንዳሳሰባቸው ጠቅሰው፥ ሃገራትም አላስፈላጊ ውጥረትን እንዲያስወግዱ ጥሪ አቅርበዋል።
አሜሪካ ባለፈው ዓርብ የኢራን ብሄራዊ አብዮት ዘብ ጠባቂ ሃይል አዛዥን በባግዳድ አውሮፕላን ማረፊያ ከገደለች በኋላ በመካከለኛው ምስራቅ ውጥረት ነግሷል።
ኢራን ለአሜሪካ እርምጃ ከባድ አፀፋዊ ምላሽ እሰጣለሁ ስትል፥ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕም አሜሪካ የከፋ እርምጃ እንደምትወስድ አስጠንቅቀዋል።
ምንጭ፦ ሬውተርስ