Fana: At a Speed of Life!

ሱዳን የባለሙያዎቹ የተጨማሪ ሃላፊነት ቢጋር ካልተዘጋጀ በቀር ውይይት መካሄድ አይችልም የሚል አቋም መያዟ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዛሬው ዕለት በበይነ-መረብ ስብሰባ አካሂደዋል።

ስብሰባው በደቡብ አፍሪካ የዓለምአቀፍ ግንኙነትና ትብብር ሚኒስትር እና የኣፍሪካ ህብረት አስፈጻሚ ምከር ቤት ሊቀመንበር ሰብሳቢነት ተካሂዷል።

ሚኒስትሮቹ የሕዳሴው ግድብ ድርድር በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ ምክከር አድርገዋል፡፡

ስብሰባው ባለፈው ሳምንት እንዲካሄድ ስምምነት ተደርሶበት የነበረው የሶስትዮሽ ስብሰባ ሱዳን ባለመገኘቷ ምክንያት ሳይካሄድ ከቀረ በኋላ የተካሄደ ነው፡፡

የአፍሪካ ህብረት አስፈጻሚ ምክር ቤት ሊቀመንበር ድርድሩን ለማስቀጠል ይረዳል በሚል ሃገራቱ ለሶስት ቀናት ከአፍሪካ ህብረት ባለሙያዎች ጋር የሁለትዮሽ ስብሰባ እንዲያካሂዱ፣ በማስከተል የሶስትዮሽ ስብሰባ እንዲካሄድ እና ውጤቱ ለሊቀመንበሯ እንዲገለጥ ሃሳብ አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያ እና ግብጽ ይህን ተቀብለው ለመቀጠል የተስማሙ ሲሆን ሱዳን ሃሳቡን ባለመቀበሏ ስብሰባው በዚሁ ተጠናቋል፡፡

ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ስብሰባ ሱዳን የሶስትዮሽ ስብሰባ እንዳይካሄድ እና ስብሰባዎች ከአፍሪካ ህብረት ባለሙያዎች ጋር ብቻ እንዲደረጉ አቋም መያዟ ይታወሳል፡፡

ሆኖም በዛሬው ስብሰባ ሀገራቱ ከአፍሪካ ህብረት ባለሙያዎች ጋር የሁለትዮሽ ስብሰባ ያድርጉ የሚለው ሃሳብ ሲቀርብ፣ ሱዳን የባለሙያዎቹ የተጨማሪ ሃላፊነት ቢጋር ካልተዘጋጀ በቀር መካሄድ አይችልም የሚል አቋም ይዛለች፡፡

ኢትዮጵያ የሱዳንን ጥያቄዎች ለመመለስ እንዲቻል በግድብ ደህንነት፣ በመረጃ ልውውጥ እንዲሁም በሌሎች ቴከኒካዊ ጉዳዮች ላይ መፍትሄ ለመስጠት ዝግጁነቷን ገልፃለች፡፡

በተጨማሪ አሁኑኑ ውጤታማ እና እንካለእንካ መርህ ላይ የተመሰረተ የመረጃ ልውውጥ ለመመስረት ፈቃደኛ መሆኗን አሳውቃለች፡፡

በቀጣይነት የአፍሪካ ህብረት የአስፈጻሚ ምክርቤት ሊቀመንበር ለአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የስብሰባውን ውጤት የሚያቀርቡ ሲሆን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ምከርቤት የሚሰጠው አቅጣጫ ይጠበቃል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.