የሀገር ውስጥ ዜና

ሽልማቱ የመከላከያ ሰራዊት ለቀጠናው ሰላም ላበረከተው አስተዋፅኦ እውቅና የሰጠ ነው – ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ

By Tibebu Kebede

January 10, 2021

አዲስ አበባ ፣ ጥር 2 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ ከጂቡቲ ህዝብና መንግስት የተበረከተላቸው የሀገሪቱ የመጨረሻ ደረጃ ከፍተኛ ኒሻን የሀገር መከላከያ ሰራዊት ለቀጠናው እያበረከተ ላለው ሰላም እውቅና የሰጠ መሆኑን ገለፁ።

በጁቡቲ የሀገሪቱ ከፍተኛ የሜዳልያ ኒሻን የተበረከተላቸው የመከላከያ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀኔራል ብርሀኑ ጁላ አዲስ አበባ ሲገቡ ደማቅ አቀባበል ተደጎላቸዋል።

ጀኔራል ብርሃኑ ማምሻውን ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮኘላን ማረፊያ ሲደርሱ የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር ቀንዓ ያደታን ጨምሮ ከፍተኛ የመከላከያ መኮንኖች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ሽልማቱ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ለቀጠናው ሰላም እያበረከተ ላለው አስተዋጽኦ እውቅና የሰጠ መሆኑንም ለኢዜአ ተናግረዋል።

መንግስት በጁንታው ላይ የህግ ማስከበር እርምጃ በወሰደበት ወቅት በርካታ የጎረቤት ሀገራት ቀጠናው ይረበሻል የሚል ስጋት አድሮባቸው እንደነበርም አስታውሰዋል።

ነገር ግን ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት የህግ ማስከበር እርምጃውን በአጭር ጊዜ በድል ማጠናቀቁ በቀጠናው ሀገራት አድናቆት እንዲቸረው አድርጓል ብለዋል።

ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ በትናንትናው ዕለት በጂቡቲ ፕሬዚዳንት ሙሉ ፍቃድ የሀገሪቱ የመጨረሻ ከፍተኛ ኒሻን ከጂቡቲ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀኔራል ዘከሪያ ሼህ ኢብራሂም እንደተበረከተላቸው ይታወቃል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!